“ከተማዋ ስታጌጥ እኛ በጨለማ ውስጥ ነን”: በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሳቢያ የተፈናቀሉ 4 ሺህ የሚጠጉ አባወራዎች የፍትህ ያለህ አቤቱታ
(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ባለው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ምክንያት ከነባር ይዞታቸው የተነሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገቢው የካሳ ክፍያ ሳይፈጸምላቸውና መሠረተ ልማት በሌለበት አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን በመጥቀስ ብርቱ ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቁጥራቸው ከ3,800 እስከ 4,000 የሚገመት አባወራዎች በ2017 ዓ.ም ሕዳር ወር ላይ “ለልማት” በሚል ከቀያቸው ተነስተው በአራብሳ ቃጥላ ማርያም ጀርባ በሚገኝ ባዶ የእርሻ ቦታ ላይ እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን ለመሠረት ሚድያ አስረድተዋል።
ይህ ሰፊ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ማህበረሰብ እንደሚገልጸው፣ የሰፈሩበት አካባቢ ውሃ፣ መብራትና መንገድን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች የማይገኙበት በመሆኑ ህይወታቸው ለከፋ አደጋ ተጋልጧል።
ከተሰጣቸው አነስተኛ የካሳ ክፍያ ላይም በወቅቱ “ለተለያዩ ጉዳዮች” በሚል ቅናሽ ተደርጎ እንደተሰጣቸውና ያገኙትንም ጥሪት ለቤት ኪራይና ለዕለት ጉርስ በማዋል አሁን ላይ ቤት ለመስራት ቀርቶ ለዕለት ምግብ የሚሆን አቅም እንዳጡ በምሬት ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ በመንግስት በኩል ቢገለጽም በሌላ በኩል ግን እንዲህ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች ከከተማው ማዕከል በማፈናቀል ወደ ዳርቻዎች የሚገፉ (Gentrification) መሆናቸው በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ስጋት ሲፈጥር ቆይቷል።
በተለይም ተፈናቃዮች ከማህበራዊ ትስስራቸውና ከስራ ቦታቸው መራቃቸው እንዲሁም በቂ የካሳ ክፍያና የመልሶ ማቋቋም ስራ አለመከናወኑ በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል።
የአሁኑ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት ጉዳዩን በግልም ሆነ በኮሚቴ በኩል ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለማመልከት ቢሞክሩም ተገቢውን ምላሽ ከማግኘት ይልቅ ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸውና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችም የሕዝቡን ድምፅ ለማሰማት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
“ከተማዋ በእኛ መስዋዕትነት በመብራት እና በአረንጓዴ ተክል ብታጌጥም የኛ ሕይወት ግን ጨልሟል” የሚሉት እነዚህ ዜጎች የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ ቀሪ የካሳ ክፍያቸው የሚፈጸምበትንና በሰፈሩበት አካባቢ መሠረተ ልማት የሚገነባበትን ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ በአስቸኳይ እንዲያሳውቋቸው ጠይቀዋል።
መሠረት ሚዲያም ይህንን የዜጎች ሮሮ በማድመጥ እና በመከታተል ጉዳዩን ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማድረስ በኩል የጋዜጠኝነት ኃላፊነቱን መወጣቱን ይቀጥላል።
| መሠረት ሚድያ |



