በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች
በምርጫው ዙርያ ያሰናዳነው ዝርዝር ማጠቃለያ እንደሚከተለው ቀርቧል። ይህ ዘገባ ሀገሪቱ ካለችበት ፖለቲካዊ፣ ጸጥታ ነክ እና ሎጂስቲካዊ ሁኔታዎች አንጻር የምርጫውን አጠቃላይ ገጽታ በጥቂቱ ተካቶበታል።
በቅድሚያ፣ የመሠረት ሚድያ ዳሰሳ እንደተመለከተው በዛሬው የምርጫ ሂደት እስካሁን በመዲናዋ አዲስ አበባ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። የመንግስት ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የምርጫው ተወዳዳሪዎች በመንግስት ሚድያዎች ሰፋ ያለ ሽፋን አግኝተዋል። ቀሪው በሚከተለው መልኩ ይቀርባል።
ሮይተርስ በዘገባው እንዳስነበበው ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ለዚህ ምርጫ የተመዘገቡ ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብልጽግና ፓርቲ ደካማ እና የተከፋፈለ ተቃዋሚ ስለገጠመው በቀላሉ አሸናፊ እንደሚሆን በሰፊው ይጠበቃል ብሏል።
ቻተም ሃውስ ባወጣው ትንታኔ ይህ ምርጫ ከ1991 ጀምሮ የብዝሃ-ፓርቲ ዴሞክራሲ ከተዋወቀ በኋላ ከተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ተወዳዳሪነት የሚታይበት ሊሆን እንደሚችል ገልጿል። ምርጫው ለህዝቡ ተጨባጭ የፖለቲካ አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ የገዢውን መንግስት ስልጣን ለማረጋገጥ እና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተቋሙ ተችቷል።
ዘ ኢኮኖሚስት የብልጽግና ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ እና ራዕይ በስፋት ዳሷል። ፓርቲው የስንዴ አዝመራን እንደ ምርጫ አርማው የተጠቀመ ሲሆን ይህ የስንዴ ዘለላ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት የሚወክል መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በቅርቡ በተካሄደ ሰልፍ ላይ እንደተናገሩት ይህ አርማ ኢትዮጵያ ወደ "የምግብ ሉዓላዊነት" እያደረገች ያለውን ጉዞ ያሳያል ብሏል፣ ይሁንና የገዢው ፓርቲን ያስቆጣ ሰፋ ያለ ዘገባ ይዞ ወጥቷል።
የቢቢሲ ዘገባ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሚዲያ በጥብቅ ቁጥጥር ስር መሆኑን እና እንደ ቢቢሲ ላሉት የዜና አውታሮች እና ሌሎች ድርጅቶች የፕሬስ ፈቃድ (Accreditation) አለመሰጠቱን ያትታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ግንቦት 24፣ 2018 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ያለውን ምርጫ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በጸጥታ ችግር ምክንያት 143 የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት ሊከፈቱ አለመቻላቸውን አስታውቋል። በተጨማሪም፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል "በተወሰኑ ቦታዎች" የድምጽ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ መቋረጡንም ቦርዱ መግለፁን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
ዶይቼ ቬለ (DW) እንደዘገበው ምርጫ ቦርዱ በጸጥታ ችግር ምክንያት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚገኙ 46 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫው እንደማይካሄድ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። በአማራ ክልል ሰሜን ምዕራብ ክፍል በሚገኙ 8 ወረዳዎች በሚሊሻዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ባለው ግጭት ምክንያት ድምጽ መስጠት አልተቻለም።
በትግራይ 38 ወረዳዎች በፌደራል መንግስቱ እና በህወሃት (TPLF) መካከል ባለው ከፍተኛ ውጥረት የተነሳ ምርጫው መታገዱን DW ገልጿል። ቢቢሲ እና ሮይተርስ በበኩላቸው፣ በ2022 ከተጠናቀቀው አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት እያገገመ ያለው የትግራይ ክልል በአጠቃላይ ከዚህ ምርጫ ሙሉ በሙሉ መገለሉን አረጋግጠዋል። ቻተም ሃውስ ይህ ውጥረት ከኤርትራ እና ሱዳን ጋር ካለው ሻካራ ግንኙነት ጋር ተዳምሮ ቀጠናዊ ግጭትን ሊያባብስ እንደሚችል ስጋቱን አስቀምጧል።
ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው በአዲስ አበባ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች በመዝገብ ላይ ስማቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው እንግልት ደርሶባቸዋል። በተለይም "49" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ ንዑስ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ ከሶስት ሺህ በላይ መራጮች የተመዘገቡ ቢሆንም በርካታ ሰዎች የምርጫ ካርድ ይዘው ስማቸው በመዝገቡ ላይ ባለመኖሩ "ስማችሁ የለም" ተብለው ወደ ቤታቸው ለመመለስ ተገደዋል ብሏል።
አዲስ ስታንዳርድ (Addis Standard) በምርጫው ዕለት የመስክ ዘገባ ለማቅረብ በስፋት ዝግጅት አድርጎ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የድርጅቱን የምዝገባ ምስክር ወረቀት መሰረዙን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ለ10 ጋዜጠኞች እና ለ2 የካሜራ ባለሙያዎች የምርጫ ባጅ (ፈቃድ) መከልከሉን ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል መተሃራ ከተማ በምርጫው ሂደት ላይ መራጮች ማንነቱ ያልታወቀና አስቀድሞ የታጠፈ ወረቀት እንዲቀበሉ እንደተገደዱ የተናገሩ ሲሆን "ማንን እንደመረጥን እንኳን አናውቅም" ብለው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል። በተጨማሪም ነዋሪዎቹ ከከንቲባውና ከታጠቁ ሚሊሻዎች በሚደርስባቸው ጫና እና የቤት ለቤት አፈና ፍራቻ የተነሳ ምንም ዓይነት ጥያቄ ማንሳት እንዳልቻሉና የህዝብ ድምጽ በግልጽ መነጠቁን በስልክ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ እና አማራ ክልልሎች ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በተያያዘ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የትራንስፖርት አገልግሎትን አሰናክለዋል። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (OLA) በኦሮሚያ ክልል የትራንስፖርት አድማ በማወጅ እና ትዕዛዙን የጣሱ ተሽከርካሪዎችን በማቃጠል የሰዎችና የሸቀጦች እንቅስቃሴን ክፉኛ አግዷል።
በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል በመንግስት ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰው ከፍተኛ ግጭት እንዲሁም ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ ወደ ክልሉ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ የትራንስፖርት እና የጭነት እንቅስቃሴዎች በመገደባቸው የበርካታ አካባቢዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና ኢኮኖሚ በእጅጉ ተጎድቷል።
| መሠረት ሚድያ |


