ቅዳሜ ምሽት የመደርመስ አደጋ ያጋጠመው የእንጨት መድረክ በምስል
(መሠረት ሚድያ)- እሁድ ጠዋት በመስቀል አደባባይ የተከናወነው የህዳሴ ግድብ ምርቃት የሰልፍ ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ እና ትርዒት ለማቅረብ በዋዜማው ሲለማመዱ የነበሩ ታዳጊዎች የመድረክ መደርመስ አደጋ እንዳጋጠማቸው መረጃ ማቅረባችን ይታወሳል።
አደጋው ከማጋጠሙ ጥቂት ቀደም ብሎ የዚህ ከእንጨት የተሰራ መድረክ ምስልን የሚያሳይ ፎቶ የደረሰን ሲሆን እስከ 18 ደረጃ ከፍ ብሎ የተሰራ መሆኑ ታውቋል። ምስሉን ይመልከቱ:
ከዚህ ጋር ተያይዞ በጥቁር አንበሳ ከሚሰሩ ዶክተሮች ለሚድያችን የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው በአደጋው የተጎዱ 80 ታዳጊዎች ወደ ተቋሙ ለህክምና በአምቡላንስ መወሰዳቸው ታውቋል።
"ይህ እኛ ጋር ያለው ብቻ ነው፣ 29 የሚሆኑት የአጥንት መሰንጠቅ ያጋጠማቸው ናቸው። ሌሎቹ ወደ አለርት ሆስፒታል እና ሌሎች የህክምና ተቋማት ሪፈር ተደርገዋል" በማለት አንድ የሆስፒታል ምንጫችን ጠቁመዋል።
በዘውዲቱ ሆስፒታልም ቁጥራቸው ከፍ ያለ ጉዳተኞች መወሰዳቸው የታወቀ ሲሆን በአጠቃላይ በዕለቱ 240 ታዳጊዎች የተለያየ ደረጃ ያለው ጉዳት እንዳጋጠማቸው እና ህይወታቸው ያለፉም እንዳሉ ታውቋል።
"ይህ ብቻ ሳይሆን አደጋው እንደደረሰ ሰምተው ቅዳሜ ምሽት በየሆስፒታሉ ሲሯሯጡ የነበሩ ቤተሰቦች ከፍተኛ ማዋከብ ደርሶብናል፣ በፀጥታ አካላት ድብደባ የደረሰባቸውም ነበሩ" በማለት በዕለቱ ቤተሰብ ሲያፈላልግ የነበረ አንድ ግለሰብ ተናግሯል።
"ገና በለጋ እድሜያቸው ጎበዝ ጎበዝ ተማሪዎችን ከየትምህርት ቤታቸው በመምረጥ መንግስት ለጎበዝ ተማሪዎች ያዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም አለ፣ ለሶስት ቀን ስለምትቆዩ ብርድ ልብስ እና አንሶላ ይዛችሁ ኑ ተብለው ስድስት ኪሎ ካምፓስ አስገብተዋቸው ነበር" ብለው ለሚድያችን ቃላቸውን የሰጡ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የመረጃ ምንጫችን ናቸው።
ምንጩ አክለውም "ከዛ አምስት ቀን ትቆያላችሁ፣ ቀጥሎ አስር ቀን ትቆያላችሁ፣ ብሎም በቃ ጳጉሜ ትሄዳላችሁ ካሏቸው በኋላ መውጣት አትችሉም በማለት ለአባይ ግድብ ምርቃት ትርዒት ታቀርባላችሁ ብለው ስልጠና አስጀምረዋቸው ነበር" ይላሉ።
ለአዲስ ዓመት በዓል ጭምር ታዳጊዎቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሳይሄዱ ተነጥለው ማሳለፋቸው የታወቀ ሲሆን ላለፉት 15 ቀናት መስቀል አደባባይ ላይ በእንጨት እስከ 18 ደረጃ በተሰራ መድረክ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸው ታውቋል።
በዚህ አደጋ ዙርያ እስካሁን በመንግስት አካላትም ሆነ ሚድያዎቻቸው የተባለ ነገር የለም።
-መሠረት ሚድያ-





18 tiered rows of bleachers!! This is absolutely crazy. Who is the engineer that designed this monster killer? Can a qualified lawyer please take this case as a class action?
🥲