በእንሴኖ ከተማ በዚህ ሳምንት የተፈጸመ አንድ አሰቃቂ ግድያ ማህበረሰቡን ከባድ ሀሃዘን ላይ ጥሏል
(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ማክሰኞ ሚያዝያ 20/ 2018 ዓ.ም ሌሊት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ምስራቅ ጉራጌ ዞን ስር በምትገኘው እንሴኖ ከተማ ውስጥ በታጣቂዎች የተፈጸመ ጥቃት የአምስት ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
ጥቃቱ በተለይ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ ያነጣጠረና እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ የተፈጸመ መሆኑን በከተማው የሚገኙ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
እነዚህ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ድርጊቱ የተፈጸመው ሌሊት 9፡00 ሰዓት ላይ ነበር። ታጣቂዎቹ በከተማው አስተዳደር ስር ልዩ ስሙ "አየር ጤና" (ወይም በሌላ መጠሪያው "ፈጦ መውጫ") ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ውስጥ ወደሚገኝ የመኖሪያ ቤት በመግባት ጥቃቱን ፈጽመዋል።
በዚህ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ እመቤት የሆኑት እናት፣ ከጎናቸው የነበሩ 3 የጨቅላ ህጻናት ልጆቻቸው እንዲሁም በወቅቱ አብሯቸው የነበረ አንድ የጎረቤት ልጅ በድምሩ 5 ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸው አልፏል።
የአይን እማኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ጥቃቱ የታቀደና በንጹሃን ላይ ያለምንም ርህራሄ የተፈጸመ ነው። ሟቾቹ በቤታቸው ውስጥ በሰላም ተኝተው በነበሩበት ወቅት መገደላቸው የማህበረሰቡን ቁጣና ሃዘን አባብሶታል።
ይህንን ዘግናኝ ድርጊት ተከትሎ የማህበረሰቡ ተወካዮች እና ሰላም ፈላጊ ዜጎች ድርጊቱን በጽኑ አውግዘዋል። "ለተገደሉት ንጹሃን ድምጽ እንሁን" በሚል የቀረበው ጥሪ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት በአስቸኳይ ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ እንዲሁም በአካባቢው እየታየ ያለው የጸጥታ መደፍረስ በዘላቂነት እንዲፈታ የፌደራል የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
እንደዚህ ያሉ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዝምታ እንዳይታለፉና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው ሚዲያዎች ሚናቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው ድባብ በሃዘን የተዋጠ ሲሆን፣ የከተማው ነዋሪዎች በመንግስት ላይ ያላቸውን ቅሬታ እየገለጹ ይገኛሉ። የጸጥታ አካላት በጉዳዩ ላይ ያደረጉት ምርመራ መኖር አለመኖሩ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።
ይህ ጥቃት በንጹሃን፣ በተለይም በእናቶችና በህጻናት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ በክልሉ የሰላም ሁኔታ ላይ ትልቅ ስጋት መፍጠሩ አልቀረም።
ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን እንመኛለን።
| መሠረት ሚድያ |



