(መሠረት ሚድያ)- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን፣ በወለጋ እንዲሁም በሞያሌ አካባቢዎች በሚገኙ ንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ እና የንብረት ውድመት አስመልካቶ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ (CBCE) የጽኑ ውግዘት እና የሐዘን መግለጫ አወጣ።
ጳጳሳቱ የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ እና የሕግ አካላት የዜጎችን ሕይወት የመታደግ፣ ንብረት የማስጠበቅ እንዲሁም የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በአስቸኳይ የመመለስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አጥብቀው ጠይቀዋል።
የጳጳሳት ጉባኤው ይፋ ባደረገው ይፋዊ መግለጫ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም በምሥራቅ አርሲ ዞን መርቲ እና ሸርካ ወረዳዎች በተፈጸሙ ድንገተኛ ጥቃቶች በርካታ ምእመናን ሕይወታቸውን ማጣታቸውን እና በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን ገልጸዋል።
ይህንን አሰቃቂ ድርጊት አስመልካቶ የተሟላ መረጃ ያገኘው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው የደረሰው እልቂትና እንግልት አጠቃላይ የሃይማኖት ማኅበረሰቡን እና አገሪቱን በጥልቅ ሐዘንና ስጋት ውስጥ የጣለ መሆኑን አመልክቷል።
የካቶሊክ ጳጳሳቱ በመግለጫቸው አርሲ ላይ ከደረሰው ጥቃት ባሻገር፣ በወለጋ እና በሞያሌ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የተከሰቱ ግጭቶችን እና የንጹሐን ዜጎችን ግድያ አሳትውሰዋል።
በነዚህ አካባቢዎች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹት አባላቱ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ መሰል አሰቃቂ ድርጊቶች በፍጹም "ሰብዓዊነት የጎደላቸው እና ተቀባይነት የሌላቸው" መሆናቸውን በመጠቆም ድርጊቱን በጽኑ ኮንነዋታል።
በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች መሰል ዘግናኝ ጥቃቶች በተደጋጋሚ መከሰታቸው አሳሳቢ መሆኑን ያመላከተው የጳጳሳቱ መግለጫ ድርጊቱ በዜጎች ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ውድመት እጅግ የከፋ መሆኑን አስገንዝቧል።
ስለሆነም መንግሥት ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ረገድ ቁርጠኛ እርምጃ በመውሰድ የሕዝቡን የደህንነት ስጋት እንዲያስወግድ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ የትኛውም ዜጋ በሰላም የመኖርና ሃይማኖቱን የመለማመድ መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ተገልጿል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ በዚሁ አሰቃቂ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ንጹሐን ዜጎች ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና በሙሉ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ዘንድ መጽናናትን የተመኘ ሲሆን የአገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና ተጎጂዎችን ለመደገፍ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በጋራ እና በትክክለኛ ሕሊና እንዲቆሙ አሳስቧል።
| መሠረት ሚድያ |



የእኛ ሲኖዶስማ በንዋይ ጥቅማጥቅም ተጠምደዋል