ያለ ሀኪም ትዕዛዝ የሚገዙ መድሀኒቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ትግበራ ተጀመረ
(መሠረት ሚድያ)- በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ (value added tax- VAT) አዋጅ ውስጥ በርካታ ከዚህ በፊት ነፃ የነበሩ ምርቶች እና አገልግሎቶች ወደ ታክስ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለዘመናት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሆነው የቆዩት ያለ ሀኪም ትዕዛዝ በህብረተሰቡ ከፋርማሲዎች እና ከሆስፒታሎች የሚገዙ መድሀኒቶች ናቸው።
ይሁንና መሠረት ሚድያ የተመለከተውና የገቢዎች ሚኒስቴር ነሀሴ 8/2017 የፃፈው ደብዳቤ በአዋጁ መሰረት ከዚህ በፊት ከታክሱ ነፃ የነበሩ መድሀኒቶች ታክስ እንዲሰበሰብባቸው ይደረጋል።
"አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት ግዜ አንስቶ በዘርፉ ተሰማርተው ግዴታቸውን ያልተወጡ አካላት ካሉ ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ እናሳስባለን" በደብዳቤው ያለው የገቢዎች ሚኒስቴር ያለ ሀኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ መድሀኒቶች ዝርዝር ከኢትዮጵያ ምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እንደደረሰው ያስረዳል።
በዚህም መሰረት ከዚህ በኋላ በማንኛውም ሰው ካለ ሀኪም ትዕዛዝ የሚገዙ ሙድሀኒቶች የ15 ፐርሰንት የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚጣልባቸው ታውቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ወደ 17 ፐርሰንት ከፍ ሊል እንደሆነ ዘገባዎች ከወጡ በኋላ የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው ዘገባ ምጣኔው 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል ብሏል።
ነባሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከምጣኔ ውጭ ሌሎች ማሻሻያዎችን በማካተት ከ3 አስርት ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ በ2017 በጀት አመት ስራ ላይ መዋሉን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከነበረው ከ12 በመቶ በላይ ድርሻ በየዓመቱ በተከታታይ እየቀነሰ ከ7 በመቶ በታች መድረሱን ጠቅሶ ከዚህ ጠቅላላ ቅናሽ 44 በመቶው የተጨማሪ እሴት ታክስ ድርሻ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
የተጨማሪ እሴት ታክስ ህጉን አሁን ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ የቀጣይ ዓመታት ለውጦች ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በመካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂው መሰረት ተሻሽሎ በ2017 በጀት ዓመት ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ብሏል፡፡
-መሠረት ሚድያ-




