በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ትናንት በተቀሰቀሰ መጠነ ሰፊ ጥቃት የ37 ምዕመናን ሕይወት ማለፉና ከ200 በላይ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን በአሰኮ ወረዳ ከትናንት ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ተነጣጥሮ በተሰነዘረ መጠነ ሰፊ እና አሰቃቂ ጥቃት እስካሁን የ37 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለመሠረት ሚዲያ ከአካባቢው የደረሰው መረጃ አመላከተ።
በጥቃቱ በአሰኮ ወረዳ በሚገኙት በጠለታ ገብርኤል እና በኩፍቴና መድኃኔዓለም አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መድረሱ የታወቀ ሲሆን ሁለት ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ 234 መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ መውደማቸውን ከአካባቢው በቀጥታ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ይህ ጥቃት ዛሬ ግንቦት 24 ቀን ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በወረዳው ስር በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 'እጅግ የከፋ' የተባለ ጥቃት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል።
ለመሠረት ሚዲያ በደረሰው ወቅታዊ መረጃ መሠረት በዛሬው ዕለት በዘዲቡ፣ በእሬቻ ሚካኤል፣ በሱንቴ ማርያም፣ በቦግዶ አቦ፣ በሌንጫ ኦዳ፣ በጂሶ እና በኳስ ድሬ ቀበሌዎች ውስጥ ጥቃቱ እየተፈፀመ ይገኛል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን በራሳቸው ኃይል መቋቋም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ስላሉ እንዲሁም ንብረታቸውና መኖሪያ ቤታቸው የተቃጠለባቸውና ለሕይወታቸው የሰጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት ወደ ጫካዎች በመሰደድ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
"ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል ባላቸው አቅም ራሳቸውን ለመከላከል ጥረት ያደርጉ የነበረ ቢሆንም የመንግሥት ካድሬዎች አካባቢውን በማረጋጋትና ዋስትና በመስጠት ስም ነዋሪውን እንዲዘናጋ በማድረጋቸው ምክንያት ሕዝቡ ለከፍተኛ ጥቃት ተጋልጧል" በማለት አንድ የአካባቢው ምንጭ በስልክ ተናግረዋል።
በዚህ ዙርያ ዛሬ ማምሻውን የወጡ ተጨማሪ ዘገባዎች ደግሞ የዚህን ጥቃት መነሻና አጠቃላይ የጀርባ ታሪክ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ይሰጣሉ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ ትኩረት ወደ አገራዊ ምርጫው ማድላቱንና በዚሁ ሳቢያ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ክፍተት የታጠቁ ኃይሎች እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በጥቃቱ ላይ መሰማራታቸው ተገልጿል።
ይህ በምሥራቅ አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በሚገኙ አካባቢዎች በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረው መጠነ-ሰፊ ጥቃት በአገራዊ ምርጫው ዋዜማና በዕለቱ የታቀደ ይመስል የተፈጸመ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በወረዳው ሥር በሚገኘው ጠላታ ጨፋ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መኖሪያ ቤቶች በተለየ ሁኔታ እየተለዩ መቃጠላቸውና ከብቶቻቸውን ጨምሮ በርካታ ንብረቶቻቸው በታጣቂዎች እየተዘረፉ መሆኑ ተረጋግጧል።
በዚህም የተነሳ ነዋሪዎቹ አካባቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለቀው ሱንቴ ወደሚባል ስፍራ ለመሰደድ ተገድደዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ ወረዳ በሚገኘው ካራ ኩፍቴና ቀበሌ የነዋሪዎች ቤቶች በተጠናከረ ሁኔታ እየተቃጠሉ በመሆኑ ሕዝቡ የመድኃኔዓለምን ታቦት በክብር ይዞ ሕይወቱን ለማዳንና ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳቱን ከቃጠሎ ለመታደግ ወደ ሱንቴ አካባቢ መሸሹ ታውቋል።
ይህ ጥቃት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ የሃይማኖት ተቋማት ላይም ያነጣጠረ እንደነበረ የተረጋገጠ ሲሆን ከ101 ዓመታት በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ ታሪካዊ መለያ ሆኖ የቆየው የጠላታ ጨፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ ወድሟል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የካራ ኩፍቴና መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎችና ልዩ ልዩ ሕንፃዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በእሳት እንዲጋዩና እንዲወድሙ መደረጋቸው ተሰምቷል።
ይህ በተደጋጋሚ ጊዜያት መሰል አሰቃቂ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙበት የሚነገረው የምሥራቅ አርሲ አካባቢ አሁንም በአገራዊ ምርጫው ዋዜማና በዕለቱ መጠነ-ሰፊ የጥቃት ሰለባ መሆኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እጅግ አሳዝኗል።
ነዋሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት በጫካዎች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን ለሕይወታቸውና ለቀሪው ንብረታቸው ምንም ዓይነት የጸጥታ ከለላ እንደሌላቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
"ድምፅ ሁኑን እባካችሁ" በማለት ለመሠረት ሚዲያ ድምፃቸውንና ምሬታቸውን ያስተላለፉት የአካባቢው ተወላጆች መንግሥትና የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ ጣልቃ በመግባት ይሄንን እየተካሄደ ያለውን ደም አፋሳሽ ጥቃትና መፈናቀል እንዲያስቆሙ፣ ለተፈናቀለውና በጫካ ውስጥ ለሚገኘው አቅመ-ቢስ ሕዝብም አስቸኳይ የሰላምና የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
መሠረት ሚዲያ በአካባቢው ያለውን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታና ተጨማሪ መረጃዎችን በቅርበት እየተከታተለ ለሕዝብ የሚያደርስ መሆኑን ይገልፃል።
| መሠረት ሚድያ |



እንደዚህ ዓይነት ዜናዎች ግን ለዓለም መዳረስ አለባቸው እኮ። እንደዚህ ዓይነት አመጾች ካሉ ምንም ዓይነት ድጋፍ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንዳይኖሩ መደረግ አለበት። ይሄ እዚህ ባለው ሕዝብ የሚቻል አይመስለኝም።