በአዳማ ከተማ ዙርያ ያሉ አርሶ አደሮች አርሶ የራሳቸውን መሬት ለማግኘት እስከ ሦስት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የጉቦ ክፍያ እየተጠየቁ መሆኑን ለመሠረት ሚድያ ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- በአዳማ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙት ደካ አዲ እና ወንጂ በተባሉ አካባቢዎች በሚኖሩ አርሶ አደሮች ላይ እየተፈጸመ ያለው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የሙስና ተግባር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ መረጃዎች ለሚድያችን ደርሰዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ እና በደካ አዲ አካባቢ ያሉ አመራሮች ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ አርሶ አደሮች የራሳቸውን መሬት ለማግኘት እስከ ሦስት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የጉቦ ክፍያ እንዲፈጽሙ እያስገደዱ ሲሆን ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል የማይችሉ ደካማ እናቶችን ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ለማጥቃት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ተብሏል።
እነዚህ አመራሮች የገንዘብ አቅም የሌላቸውን እናቶች ለማሰር ሲሉ "መሬት በጨረቃ ሸጣችኋል" የሚል በኮምፒውተር የተቀነባበረ የሀሰት ሰነድ እንደ ማስረጃ በመጠቀም ንጹሃንን ለእስር እና ለእንግልት እየዳረጉ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከአምስት ቀን በፊት ሌሊት በመኖሪያ ቤቶች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ለገለልተኛ ሚዲያዎች መረጃ ሰጥታችኋል በሚል ምክንያት በሕፃናት ላይ ጭምር ድብደባ መድረሱ ታውቋል።
"በወቅቱ የፀጥታ ኃይሎች ቤታቸውን ሰብረው በመግባት በፈጸሙት ድብደባ ሁለት ሕፃናት በጽኑ ቆስለው የሚገኙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ያለ ምንም የሕክምና እርዳታ በእስር ቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉ ጉዳዩን ይበልጥ አሰቃቂ ያደርገዋል" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት አንድ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
በወንጂ ወረዳ የባቴ ገርማማ ዞንም የገጠር ኮሪደር ልማትን ሽፋን በማድረግ አርሶ አደሩን ከመሬቱ የማፈናቀል ስራ እየተሰራ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረው የአካባቢው አመራሮች ወጣቶችን ሞራል በሚነኩ ስድቦች በማንቋሸሽ እና "ወደ ጫካ ግቡ" የሚሉ ወደ ግጭት የሚያመሩ ንግግሮችን በመጠቀም ሕዝቡን ለከፋ ችግር እየገፋፉት ይገኛሉ ተብሏል።
የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ለተጎጂዎች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የቀረበውን አቤቱታ "የጠላት ሚዲያ ወሬ ነው" በማለት እያጣጣሉት እንደሚገኙ የሰማን ሲሆን ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎችንም "መሬት ስር እናስራችኋለን" በሚል ማስፈራሪያ ድምፃቸውን ለማፈን እየሞከሩ ነው ተብሏል።
"በአሁኑ ወቅት ለሕይወቷ ሰግታ የተደበቀች አንዲት ተጎጂ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አቤቱታ ለማቅረብ ጥረት እያደረገች ሲሆን የታሰሩት እናቶችና ሕፃናት ያሉበት ቦታም በግልጽ ይታወቃል። ይህ በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ በአስቸኳይ እንዲቆም እና የታሰሩት ሕፃናት የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት አግዙን" በማለት ሌላ የአካባቢው አዛውንት በስልክ ለሚድያችን ተናግረዋል።
ለዘገባው ግብዓት የሚሆኑ የተጎጂዎች እና የኃላፊዎች ስልክ ቁጥሮችም ለመገናኛ ብዙሃን ቀርበዋል። የአካባቢው ሀላፊዎች ግን ጥያቄውን ከሰሙ በሗላ ስልክ ዘግተዋል።
| መሠረት ሚድያ |


