የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የትናንት የመሠረት ሚድያን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ በ354 የነዳጅ የማደያ ባለቤቶች ላይ ክስ መስርቻለሁ አለ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን በትናንትናው እለት ባስነበበው አንድ የምርመራ ዘገባው ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ አሻጥር በጋምቤላ ክልል እየተፈፀመ መሆኑን ጠቁሞ ነበር።
ከንግድ ቢሮ ሀላፊዎች ጀምሮ እስከ የክልሉ ፕሬዝዳንት በሚሳተፉበት መልኩ የሚካሄደው ይህ ህገወጥ የነዳጅ ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ አሁን ላይ በግልፅ አንድ ሊትር ናፍጣ ከ220 ብር እስከ 280 ብር በነዳጅ ማደያ ውስጥ በጄሪካን እየተሸጠ መሆኑን መረጃ አቅርበን ነበር።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ይህን ዘገባ ተከትሎ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርገዋል በተባሉ 354 ተጠርጣሪ የነዳጅ የማደያ ባለቤቶች ላይ ክስ መስርቻለሁ ብሏል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲበራ ፉፋ ለኢቢሲ እንደተናገሩት ማደያ ውስጥ ነዳጅ እያለ የለም ብለዋል በተባሉ እና ከማደያ ለተሽከርካሪዎች መሸጥ ሲገባቸው በጀሪካንና በበርሜል ሲሸጡ የተገኙ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከታሪፍ ማሻሻያ ፍላጎት ጋር በተያያዘ በወራት መጨረሻ ላይ በማደያዎች አካባቢ የሚታዩትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሕግ ማስከበር ስራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
በተደረጉ ጠንካራ የቁጥጥር ስራዎችም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በወራት መጨረሻ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የተሸከርካሪ ሰልፎችን መቀነስ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና መሠረት ሚድያ የተቀበላቸው በርካታ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የተሽከርካሪ ሰልፎች በመጠኑ ቢቀንሱም ህገወጥ የነዳጅ ሽያጩ መቀጠሉን ያሳያሉ።
ከነዳጅ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች በኢትዮ ቴሎኮም በኩል የለማውን ጂፒኤስ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አቶ ዲበራ ጠቁመዋል።
መረጃን ከመሠረት!



