
(መሠረት ሚድያ)- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን ሮቤ ወረዳ እንዳቶ ቀበሌ ዛሬ ጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም ከማለዳው 11 ሰዓት ጀምሮ ታጣቂዎች በፈጸሙት አሰቃቂ ጥቃት የበርካታ ንጹሐን ዜጎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።
እስከ አሁን ድረስ ከተገደሉት ንጹሐን መካከል የ34 የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ህይወት አልፎ አስክሬን ተፈልጎ በእንዳቶ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መሰብሰቡን ማህበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ዘግቧል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን የመረጃ ምንጮች እንደተረጋገጠው በስፍራው የተፈጸመው ጥቃት እጅግ አሰቃቂ እና ድንገተኛ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር አሁንም ሊያሻቅብ እንደሚችል ተጠቁሟል።
የሮቤ ወረዳ እንዳቶ ቀበሌ ከሸርካ ወረዳ ጋር አዋሳኝ እንደመሆኑ መጠን ከቀናት በፊት ማለትም ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሸርካ ወረዳ ከተፈጸመው ተመሳሳይ ዘግናኝ ጥቃት በኋላ ዛሬ ደግሞ በእንዳቶ ቀበሌ ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃትና ስጋት ፈጥሯል።
ዛሬ ጥቅምት 26 ቀን የተከሰተውን አሰቃቂ ጥቃት ለማስቆም እና የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ ወደ ስፍራው ያመሩ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አካላትም የዚሁ ድንገተኛ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ጥቃቱን ያደረሱት ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ በርካታ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በጥቃቱ ሳቢያ መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት ተጎጂዎች እስካሁን ድረስ በቂ የሆነ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለመቻላቸው ተገልጻል።
ከሰው ሕይወት ማለፍ እና አካል ጉዳት ባሻገር የታጠቁት ኃይሎች በፈጸሙት ውድመት በርካታ የንግድ ተቋማት እና የነዋሪዎች ንብረቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውና መቃጠላቸው ተረጋግጧል። በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የሰፈነ ሲሆን የምእመናኑ ሕይወት በአስቸኳይ የሚታደግበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥሪ እየቀረበ ይገኛል።
በምሥራቅ አርሲ ዞን ሮቤ ወረዳ እንዳቶ ቀበሌ የምእመናን ግድያ እና እንግልት የጀመረው ከጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደነበር የሚያስታውሱት የአካባቢው ነዋሪዎች የዛሬውን ጥቃት ከቀደሙት መሰል አሰቃቂ ድርጊቶች ጋር በማያያዝ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆነው ሁኔታዎችን ወደ ኋላ መለስ ብለው አሳትውሰዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምሥራቅ አርሲ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በንጹሐን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ የቆዩት መሰል ጥቃቶች አሁንም ቢሆን አሳሳቢ መልክ ይዘው መቀጠላቸውን መረዳት ተችሏል።
ነዋሪዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎች የሕይወት ደህንነት እንዲጠበቅ ጥብቅ የደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ በመማፀን ላይ ይገኛሉ።
| መሠረት ሚድያ |

