ኢትዮጵያ በአለማችን ከሚካሄዱ ግዙፍ ኮንፈረንሶች አንዱ የሆነውን ኮፕ32 ለማስተናገድ ልትመረጥ መሆኑ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ በአለማችን ከሚካሄዱ ግዙፍ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶች አንዱ የሆነውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ጠባይ ስብሰባ (Conference of the Parties- CoP) እንድታስተናግድ ጫፍ መድረሷ ታወቀ።
ከአንድ አመት በኋላ የሚካሄደውን ኮንፈረንስ ኮፕ31 ለማስተናገድ ተርኪዬ እና አውስትራሊያ እየተፎካከሩ ሲሆን ከሁለት አመት በኋላ ላይ የሚካሄደው ኮፕ32 ግን ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዘንድሮ በብራዚል እየተካሄደ ያለውን የስብሰባ አጀንዳ ጠቅሶ ሬውተርስ እንደዘገበው ተሳታፊ አገራት ኢትዮጵያ ኮፕ32ን እንድታዘጋጅ በመርህ ደረጃ ተስማምተዋል፣ ይህንንም በብራዚል እየተካሄደ ያለው ኮፕ30 ፕሬዝደንት አንድሬ ኮሬያ ዶ ሎጎ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የአስተናጋጅነት ምርጫ በተሳፊ ሀገራት እንደሚደገፍ የሚጠበቅ ሲሆን እሱም በዛሬው ዕለት እንደሚፈፀም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የአየር ጠባይ ስብሰባውን ለማስተናገድ ጥረት ማረግ የጀመረችው መስከረም ወር ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከናይጄሪያ ጋር ፉክክር መደረጉ ተጠቅሷል። ይሁንና የአፍሪካ ሀገራት ቢሮ ኢትዮጵያን መምረጡ ታውቋል።
የኮፕ ስብሰባዎች በአለም ዙርያ በተራ እየተዟዛረ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮውን ስብሰባ ብራዚል እያስተናገደች ትገኛለች።
በስብሰባው ላይ እንደ አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ ያሉ ሀገራት መሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎችም ይታደሙበታል። በዘንድሮ ስብሰባ ላይ የ60 ሀገራት መሪዎች የተገኙ ቢሆንም የአሜሪካው ፕሬዝደንት አለመገኘታቸው ታውቋል።
የኮፕ ኮንፈረንሶች ሀገራት በአመት አንዴ ተሰባስበው አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የአየር ጠባይ ለውጥ ዙርያ ያለውን ሁኔታ የሚገመግሙበት፣ ስምምነቶችን የሚፈፅሙበት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቀጣይ እርምጃዎችን የሚያዘጋጁበት ነው።
ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ካላት ልምድ ባለፈ በቅርብ አመታት በርካታ ችግኞችን በመትከል ያሳየችው እምርታ ተመራጭ እንዳረጋት ታውቋል።
-መሠረት ሚድያ-



