ተስፋ የሌለው የአዲስ ዓመት ምኞት
በተስፋዬ ወልደዮሐንስ ሀይሌ ለመሠረት ሚድያ
ትንሽ ቦታ
፠፠፠፠
ብንጣላ መታረቂያ
ብንታረቅ ለመጣያ
ብንታሰር ይቅር ማያ
ይቅር ብንል መታሰሪያ
ትንሽ እንተው ባዶ ቦታ።
ጥግ ድረስ የለም ሥራ፤ ጥግ ድረስ የለም ፋታ።
በልባችን ደግ በኩል፣ እንፈልግ ባዶ ቦታ
የጳጉሜ ዓይነት ትንሽ ቦታ
ለዘመን መለዋወጫ። - ነብይ መኮንን
(መሠረት ሚድያ)- ከባህር ዳር ወደ ማርቆስ ለስራ በሄድኩበት ጊዜ የመኪና እርዳታ ጠይቀውን የጫንናቸው ሁለት ለጋ ወጣቶች ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረውና በደመቀው ወሬያችን ለእኔ የስራ ለእነሱ ደግሞ የነፃነት መውጫ ያሉትን ቡድን ሊቀላቀሉ የሚያደርጉት ጉዞ ነበር።
ስለቤተሰባቸው ሲነግሩን አንደኛው አራስ ሚስቱን ጥሎ ሌላኛው ደግሞ ከወላጆቹ ቤት እመለሳለው ብሎ የወጡ ናቸው።
ከወላጆቹ ቤት መጣሁ ብሎ የወጣው ወጣት ሲያጫውተን እናቱ እንደምትናፍቀው ነግሮን “ዘጠኝ ልጆች አሏት ከሳር ጎጆ ላይ አንዱ ቢመዘዝ ምን ይሆናል? በእነሱ ትጽናናለች፤ እኔ የአቅሜን ማድረግ ካልቻልኩ ሁላችንም እጣ ፈንታችን ደመከልብ መሆን ነው” አለን፡፡
ወዲያው “እዚች መገንጠያ ላይ ጣለን” ብለው ተሰነባብተን ሄዱ። ዛሬ የትና እንዴት ናቸው? መረጃው የለኝም።
ከትግራይ ጦርነት ማብቃት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀሌ ዩንቨርስቲ አንድ ስልጠና ለመስጠት አቅንቼ ነበር። የዩንቨርስቲ መምህር የሆነው የስልጠናው አስተባባሪ ወደ መቀሌ ከጦርነቱ በኋላ መምጣቴን አውቆ “እስኪ ላስጎብኝህ” ብሎኝ ጥቂት ቦታዎችን ተመለከትኩ።
እግረ መንገዴን ከጦርነቱ አንድ ዓመት በፊት ያየሁትንን የሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየምን ለመጎብኘት ጎራ አልን። ጊቢውን እንደዘለቅን አምስት ወጣቶች ከተቀመጡበት ተነስተው ፎቶግራፍ መነሳት እንፈልግ እንደሆን ጠየቁን። ሁለቱ ወጣቶች እግሮቻቸውን ሶስተኛው አንድ እጁን አጥተዋል።
ተረኛ ከሆነው ወጣት ጋር በፎቶ ስንት አንደሚያስከፍለን ተስማምተን ወደውስጥ በመዝለቅ ለማስታወሻነት ፎቶግራፎችን ተነሳን።
ወደሙዚየሙ መንገድ ስንጀምር በሚገዳደር አማርኛ “ጋሼ የመጀመሪያህ ካልሆነ አሁን የምታየው የምታውቀው ሙዚየም አይደለም” አለኝ። አንዳለኝም ሙዚየሙ ወና ሆኗል።
በውስጡ ከጦርነቱ አንድ ዓመት በፊት ያየኋቸው ነገሮች በቦታው የሉም፤ ከዛ ይልቅ ሰፍሮ የነበረው ጦር ለማስታወሻነት በግድግዳዎቹ ላይ የፃፋቸው ጽሁፎች፣ የውስጥ ልብሶችና የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሎች እዚህም እዚያም ይታያሉ።
በጦርነቱ አካላቸውን አጥተው አእምሮአቸው ተጎድቶ ያገኘኋቸውና መቀሌ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለሶስት ቀናት ያሰለጠንኳቸው ወጣቶች ለቀናት እረብሸውኝ ነበር።
ባለፉት ዓመታት ጦርነት ባልተለያት ሀገርና ምድር ወጥቶ መግባት፥ ዘርቶ ማጨድ፥ የሰላም አየር መተንፈስ ቅንጦት እየሆነ ለልጆች የትምህርት ደጃፎችን፥ ለወጣቶች የስራ በሮችን ከማንኳኳት ይልቅ በተቃራኒው እየኖሩ ስጋት ላይ መውድቅ ሆኗል።
የሰላም የውይይት በሮች እየተዘጉ የመሳሪያ ሃይል አቅሙ ጎልብቶ፤ ህዝቡ ዛሬን ቢያልፍ እንኳ ነገ በስጋት የሚጠብቀው ቀን እየሆነበት ቀን መግፋት ግድ ብሎታል። ማብቂያቸው ያልታወቀው በትግራይ፥ በአማራ፥ በኦሮሚያ የተነሱ ግጭቶች በርካቶችን በስሜት፥ በአካልና በህይወት ዋጋ አስከፍለዋል። አሁንም በየቀኑ እያስከፈሉት ይገኛሉ።
ቀጣዩ የሚንኳኳውን በር አልያም ሟች ማንም ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ ቀን ይገፋል።
የችግሮቹ ምንጮች ላለፉት ዓመታት በየአካባቢው እየተነሱ መልስ ያላገኙት የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች ሲሆኑ አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ የጠፉት የውይይት፣ የንግግርና የድርድር ሀሳቦች ወደጎን ተገፍተው ስለመሄዳቸው ዓይነተኛ መገለጫዎች ናቸው።
ህዝብን አስተባብሮ ቡድንን አደራጅቶ ይህንን ጉዳይ መፍቻ መንገዳችን አንድና አንድ ጦር መሳሪያና ሀይል ነው የሚል ማህበረሰብ በየቦታው እንደየመሰባሰቢያው ጉዳይና ኣላማ በመደራጀት ህግ አስከባሪውን መግጠም ከተጀመረ ድምፁ መሰማት ያለበት ማህበረሰብ መኖሩን የግድ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ሀገር በሰላም ውላ እንድታድር ህጋዊነት ሰላምና ፀጥታ ከህግ የበላይነት እንዲሁም ከፍትህ መስፈን ጋር የዜጎችንም ሆነ የሀገሪቱን ህልውና የማስጠበቅ ሃላፊነት መንግስት በዋነኝነት ከሚስታቸው የሃላፊነትና የግዴታ ምሰሶዎች አንዱ ነው።
እናም የለውጡ መንግስት ባለፉት ሰባት አመታት ይህንን ሃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ በየቦታው የሚለኮሱ ተቃውሞዎችን እንደ ስልጣን ማራዘሚያ መጠቀምን የመረጠ ይመስላል።
መንግስትና በሃላፊነት ላይ የሚገኙ አካላት፥ ሚዲያውና የዲጅታል ሰራዊቱ፥ እንዲሁም ካድሬው የየእለት ስራቸው ምንም ለውጥ በማያመጡ፥ የህብረተሰቡን የሰላም ጥያቄና የኑሮ ውድነት በማይመልሱ የመግለጫ ጋጋታዎች ላይ ተጠምደዋል።
ቤተመንግስቱም በውበት፥ በህልምና ህዝቡ በማይኖረው፥ ባልታየውና አብሮት ማለም ባልቻለው ብልጽግና ውስጥ መሸሸግን ምርጫው አድርጓል። የኑሮ ውድነቱን እየታገለ ላለ ዜጋ ደህንነቱ ሌላኛው ፈተና ሆኖ ተጋርጦበታል። እነሆ ካለፉት ዓመታት በመቀጠል ይህንን እና መሰል ሁነቶችን ያስተናገድንበትን ዓመት ማገባደጃው መቁጠር ጀምረነዋል።
የሚያልፍ አይመስልም ያልነውንና መስከረም ብለን የጀመርነውን ዓመት አገባደን፤ በቁጥር አሻግረን ለሌላ አምላክ ቢፈቅድና ብንኖር ብለን ለምናሰበው ሌላ መስከረም አሻግሮ ሊያስረክበን የቀናት ቆይታ ብቻ ቀርተውታል፡፡
2018 ዓ.ም ከፊታችን እንኳን አደረሳችሁ መጣሁ መጣሁ እያለን ነው፡፡ አደይ አበባን በፀሐይ ብርሃን ታጅባ ልንመለከት ዓይኖቻቸን መናፈቅ ላይ ደርሰዋል፡፡ የጊዜ መንጎድ ድንቅ ነው፡፡ በብርሃን የተቀበልነውን አዲስ ዓመት በጨለማ እንሸኘው ዘንድ በብርሃን ደግሞ ሌላ አዲስ ዓመት እንድንቀበል ተፈጥሮ ግድ ትለናለች፡፡
ስንኖርበት የነበረውን ቁጥር ቀይረን አሮጌውን በአዲሱ ተክተን ቁጥር አክለን፣ በብርሃን፣ ደስታና በፀሃይ መናፈቅ ውስጥ አዲስነቱን በአደይ አበባ አጅበን አንቀበላለን፡፡ ይህ አንድ ብለን የምንጀምረው መስከረም ተጉዞ ከጳግሜ ደጃፍ ያደርሰናል፡፡
የልጅነት የአዲስ ዓመት የትምህርት ቤት መከፈት ጉጉት፣ በጭጋግ ከተሞላው፣ በረዶና ዝናብ ከማያጣው ብርሃን ወደሚቀበለው ዓመት የነበረኝን ጉጉት የእንኳን አደረሳችሁ የባህል ጭፈራውን፣ የየቤቱ የአዲስ ዓመት ዝግጅትን፣ የገበያውን ወከባ፣ ትዝታውን ተሻግሬአለሁ፡፡
እንዲያውም ዛሬ “ይህ ዓመት ካለፈው አዲስ ዓመት ምን የተለየ ነገር ይዞልን ይመጣልን ወይንም ይመጣብን ይሆን?” የሚል አንፃራዊ ጥያቄ እንዳነሳ እድሜም ሳይሆን አይቀርም ይጎተጉተኛል፡፡
ያለፉት አመታት በኢትዮጰያ ከእፎይታ ይልቅ ስጋት፣ ከመልካም ነገር ይልቅ መጥፎ ጉዳዮች፣ ከመሻሻል ይልቅ የከፉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ እያየን እና እየሰማን የመጣንባቸው ዘመናት እየሆኑብን ሰላም፣ ደህንነትና መፃኢ ተስፋን መጠበቅ እርግጠኛና ተገማች አለመሆኑን አስከትሎ በየቀኑ “ወቸው ጉድ?” የሚያስብል ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
በየቦታው የተከሰቱ ግጭቶች፣ የፖለቲካው መመሰቃቀል፣ ለመኖር፣ ወጥቶ ለመግባት የሰላም ስሜት ማጣት፣ ደህንነት ያለመሰማት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ በርካታ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ለማጠናቀቅ ቀናት የቀሩትን 2017 ዓ.ም የተፈታተኑ አንኳር ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በርካቶችን በተፈጥሮ አደጋ ያጣንበትን ያህል በቁጥር ከፍ ያሉትን ደግሞ በሰው ሰራሽ ችግሮቻቸን ከጎናችን ያጣንበት ዓመትም ነበር፡፡
ውጤቱም በርካቶችን በራቸውን አዘጋ፣ ሟቾች ለቤተሰቦቻቸው የእግር እሳት ሆኑ፣ ለአካባቢቸው ደግሞ የሚቆጩ ሰዎች ሆነው እንዲያልፉ አድርጓል፡፡
ሀገር በእኔ ትውልድ ውስጥና ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ ችግር አዙሪት ሆኖባት፣ ሁሉም ነፃነት ፈላጊ ሁሉም ነጻ አውጪ ብሎም ተፈላጊው ነፃነት በውይይት ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ የሚገኝ ተደርጎ የተቆጠረ አስተሳሰብ መሆኑን መመልከት ግድ እየሆነባት፣ የዜጎችን ህይወት በማስያዝ የሚገፋ የራስ እውነት መፈለጊያ መድረክ ከሆነች ሰነባበተች፡፡ ክስተቱን ለሚመለከት መቋጫው ቅርብ ይሆናል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል፡፡
መንግስት ሁሉን አካታች፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ መደላድሎችን ከማመቻቸት ይልቅ የእኔ ብቻ አውቅልሃለው መርህ በመያዝ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል በሚል የፖለቲካ እሽክርክሪት ውስጥ ራሳቸውን ብቻ የሚመለከቱ የፖለቲካ ልሂቃንን ይዞና የህዝብን እሮሮ ሲቃ፣ እንግልትና መከራ ከመጤፍ የማይቆጥሩ አመራሮችን ሰግስጎ፤ ምርጫን ህጋዊ መሳሪያ በማስመሰል የስልጣን ማስቀጠያ መንገድ ብቻ ለማድረግ መንቀሳቀስን ትልቅ ጉዳይ ካደረገው ሰነባበተ፡፡
ብሔር ለአዳዲስ አስተምሮቶች፣ ለዲሞክራሲ ግንባታ፣ ለአብሮ መኖር ትስስሮሽ ከመጠቀም ይልቅ ለፖለቲካ ጥቅም መሸሸጊያ፡ የበዳይና ተበዳይ ትርክት መስሪያ መሳሪያ ሆኖ መገልገልን የመረጥንበት፣ መርጠን ካልተፈጠርንበት ቡድን ጋር ማንነት ጥላቻ መውገሪያ የማዕረግና እልቅና ማግኛ የመሆን ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ባለጊዜ አደርጎብናል።
ይህንን ፈተና ይዘን 2018 ዓ.ምን ለመቀበል ጉድጉድ ላይ ባለንበት ወቅት “ኢትዮጵያ ሆይ የሚመጣው ዓመት ምን ይግጠምሽ?” ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ለእኔና ለልጆቼ የምትሆነውን ሀገር በአይነ ልቦናዬ እስላለሁ፡፡
ከታች የገለጽኳቸው አራት ቁልፍ ሀሳቦች ቢሳኩላት ምን አልባትም የተሻለች ሀገር እንደምትኖረን ተስፋ በማድረግ “ኢትዮጵያ ሆይ የአዲስ አመት መልካም ምኞቴ ይህ ነው” እላታለሁ፡፡
የተደቀኑት አፈሙዞች ወደ መሬትሽ ይውረዱ፣ ያዘቅዝቁ
ግጭት እዚህም እዚያም መገለጫ በሆነበት፣ አፈሙዞች ወደፊት ተሰድረው የሰውን ህይወት በሚቀሙበት ሀገር ውስጥ የዛሬው ልጆች፣ መጪው ትውልድ ነገ በተስፋ አይታያቸውም፡፡ የውይይትና ንግግር ትርጉም ይርቅበታል፡፡
ሁሉንም ነገር በጠመንጃ አፈሙዝ ውስጥ የማሰብ፣ ሃይል የሁሉም ነገር ምንጭነት የትውልዱ መገለጫ ይሆናል፡፡ በየቦታው ያሉ ግጭቶች ምንጫቸው ወደ ውይይት መጥተው ተኩስና የጥይት ድምፅ ርቀው መንደሮቹ ሰላም ወርዶባቸው ፀአዳ የለበሱ፣ በፈገግታ የታጀቡ ገፆችና የሚሰጡ እጆች የምናይበት፣ አፈሙዞች የሚተፉት ድምፅ በደስታ ሲቃዎች የሚቀየሩበት ዓመት እንዲሆን።
ወጥቶ መግባት የማያሳስብበት፣ የዜጎች ደህንነትና ሰላም ተጠብቆ መመልከት
መታሰር፣ መሰወር፣ መጥፋት፣ መታገትና መገደል በየእለቱ በሚመስል ሁኔታ በመገኛኛ ብዙኃን የምንመለከትበት፣ “የማህበራዊ ሚዲያው እዚህም ደረሰ” እያልን የምንመለከትበት መድረክ ሆኗል፡፡
ዜጎችን ለማስለቀቅ ከግለሰቦች የመንገድ ልመና እስከ እምነት ቤቶች የዘለቀ እንባ፣ ዋይታና ሰቆቃ የበዛበት፣ ዜጎች ወጥተው ስለመመለሳቸው እርግጠኛ የማይሆኑበት፣ የቱጋ ምን እንደሚሆኑ ዜጎች ደህንነታቸው ምን እንደሚሆን ጥያቄቸው በርትቶ የንግድ እንቅስቃሴ የተገታበት፣ ለቅሶ ተገኝተው ከጎናቸው ያሏቸውን የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን መቅበር አለመቻል የመሳሰሉ በርካታ ችግሮችን አስተናግደናል፡፡ ይህ ዓመት እዚህ ጋር ብሄድ ይህ ይገጥመኛል ብለው የማይጨነቁበት፣ በሰላም ካሰቡት ቦታ የሚደርሱበትና የሚመለሱበት ወጥቶ መግባት የማያሳቅቅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለው፡፡
መነጋገር መደማማመጥ መወያት የሃሳብ ልዕልናን ጠረጴዛ ላይ ማየት
ሁልጊዜም ከዘመን ጋር የሚቀያየር ፖለቲካዊ ትርክት፣ ፍላጎትና ተግባር እንደሚኖር በየትኛውም ዓለም የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካዊ ስነ ምህዳር ውስጥ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ የሃሳብ ልዩነቶችን ለመስማት ብዝሃነትን ለመቀበል ልዩነቶች ላይ መስራት እየራቀን፣ በተቃራኒው አለመደማመጥ ‘እኔን ብቻ ስሙ’ ‘እኔ ብቻ ልክ ነኝ’ የሚል መድረክን መፍጠርን ተያይዘነዋል፡፡
በተለይም ደግሞ በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል እውቀትና ሃሳብ ቦታ እያጣ፣ ስሜትና እኔ ብቻ እየገነነ መመልከት የእለት ተእለት ስራችን ሆኗል፡፡ ያለመነጋገር፣ ያለመደማመጥ ለውጥን ማሰብ ሩቅ ስለሚሆንብን በሮቻቸን ለሃሳብ ልዩነቶች ክፍት የሚሆኑበት ጠረጴዛችን ለውይይት መዳረሻዎቻችን ይሆኑ ዘንድ እመኛለሁ፡፡
አድር ባይነት ተወግዶ ለሀገር የሚሰራ ትውልድን መገንባት
መንግስታዊ ስርዓት ይሄዳል፣ መንግስታዊ ስርዓት ይመጣል፡፡ ሰዎች ይሄዳሉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ሀገር የብዙዎች መሰባሰቢያ ግለሰቦች ትውልድ ማፍሪያና ማስቀጠያ ገናናነትንና ታሪክ የማቆያ ምድር ናት፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አድርባይነት፣ በፊትለፊት መውደቅ “እኔ” እና “ዛሬ” ብቻ የሚል የጥቅመኝነት፣ ቡድንተኝነትና ምሁራዊ አድርባይነት መስፋፋት በሁሉም መስኮች ተስፋ እንድንቆርጥ እያደረገን ይገኛል፡፡ ሰው በችሎታው፣ በአቅሙና በእውቀቱ የሚጠበቅበት ቦታ ሲገኝ ያስደስታል፡፡
ህሊናውን መሳሪያ አድርጎ የሚሠራው እንዳንዱ ተግባር ደግሞ ለነገ በትውልዱ ለመታወስ ሚ ሃዉልትን ለማቆም እድል ይሰጠዋል፡፡ ታሪክ ይዘክረዋል፡፡ እውነት አደባባይ እንድትቆም፣ ለሌሎች ማሰብን ለሀገር መትረፍን፣ ለእውቀት፣ ችሎታና አቅም ቦታ የምንሰጥበት እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
እንደመውጫ
ሁልጊዜም ቀናትን እንደአዲስ መኖር መልመድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ትላንት፣ ከትላንት በስቲያ፣ የዛሬ ሳምንት፣ ወር፣ ዓመት ነበር ሆነዋል፡፡ አልፈዋል። ላይመለሱ ጥለውን ሄደዋል፡፡ ነጉደዋል፡፡ መነሻችን እነሱ ነበሩ፡፡ መድረሻችን ግን ዛሬና ነገ ናቸው፡፡ የኋላው ሊጎትትን አይገባም ሊያስተምረን ግን ፍፁም ትክክል ነው፡፡
ዛሬ አዲስ ቀናችን ነው፡ ብሎ መጀመርን መለማመድ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ ያለበለዚያ ካለፉት ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት፣ ዓመታት፣ የተለየ አዲስ ነገርን እንጠብቅ፡፡ ተስፋን እናድርግ፡፡
መልካም አዲስ ዓመት ከምንወዳቸው ጋር!
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-




