(መሠረት ሚድያ)- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በቅርቡ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃትና ግድያ በመቃወም ዓለም አቀፍ ተቋማትና የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች መግለጫ መስጠት ጀምረዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እና የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ባወጡት መግለጫ በሁኔታው በእጅጉ ማዘናቸውንና ስጋት እንደገባቸው አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ በመግለጫቸው "በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በንጹሃን ዜጎች ላይ ያላመለከተ ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጹ ዘገባዎች በእጅጉ አሳስበውኛል። ዩናይትድ ስቴትስ በሃይማኖት፣ በብሔር ወይም በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጸሙ ማንኛውንም ዓይነት የሃይል እርምጃዎች አጥብቃ ታወግዛለች። በየትኛውም ወገን ላይ የሚፈጸሙ መሰል አሰቃቂ ጥቃቶች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል" ብለዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ሁኔታው አጣርቶ ጥቃቱን የፈጸሙትን አካላት በህግ ፊት እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው (X) ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በአርሲ ዞን በደረሰው የሰው ህይወት ማጣት በእጅጉ መደንገጣቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አርሲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ከጎበኟቸው ቦታዎች አንዱ እንደነበር አስታውሰው ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል። በተጨማሪም ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ለማጣራትና ጥፋተኞችን ለመለየት የሚደረጉ ጥረቶችን ሀገራቸው ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮችን ኢላማ ባረገ መልኩ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ በርካታ ኢትዮጵያውያን በ 'X' (ትዊተር) ገጽ ላይ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
ዜጎች በየገጻቸው በሚያሰራጩት መልዕክት ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ለተጎጂዎች ፍትህ እንዲሰጥና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሁም ድርጅቶች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ ከቀናት በፊት የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የሪፐብሊካኖች የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ (GOP) አባላት በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አርሲ ዞን ውስጥ ከ60 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያና ጥቃት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መረጃ አጋርቶ ነበር።
ኮሚቴው በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልእክት “በኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረው ተከታታይ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሏል። ይሁንና ኮሚቴው በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ከዚህ ጥቃትና ሁከት የሚጠበቁበትን እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም ለሕግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸው ማሳሰቡ አነጋጋሪ ሆኗል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ምዕመናኑ ሲገደሉ ግጭት ተቀስቅሶ ሳይሆን በመኖርያ ቤታቸው እንዳሉ መገደላቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
| መሠረት ሚድያ |



ኤርቪን ማሲንጋ የሚባል አጋሰስ የት ነበር እስካሁን
እውነት ጉሮሮውን አንቆ ሲይዘው ነው መግለጫ ያወጣው
"ያላመለከተ ጥቃት " ምን ማለት ነው Mr Donkoro Elias