በዳውሮ ዞን በርካታ ህዝብ በወባ በሽታ ህይወቱ እያለፈ መሆኑ ተሰማ፣ ጤና ጣብያ ሞልቶ ህዝብ ዛፍ ስር ተኝቶ እንደሚታከም ታውቋል
(መሠረት ሚድያ)- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ስድስት ዞኖች መካከል አንዱ በሆነው የዳውሮ ዞን ውስጥ በቅርብ አመታት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የወባ ወረርሽን ተከስቶ የበርካታ ሰው ህይወት እያለፈ መሆኑ ታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለመሠረት ሚድያ ያቀረቡት ማስረጃ እንደሚጠቁመው በተለይ በዞኑ ጌና ወረዳ ውስጥ የወባ ወረርሽኙ ብዙ ሰውን በሞት እየነጠቀ ይገኛል።
በአካባቢው ከ80 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚያስተናግድ አንድ የጤና ጣቢያ ብቻ እንዳለ የታወቀ ሲሆን ሕብረተሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ በወባ ወረርሽኝ መጠቃቱን ተከትሎ ከአቅም በላይ ሆኔታ መፈጠሩ ታውቋል። ይሁንና የዞኑም ሆነ የክልሉ መንግሥት ዝምታን መርጧል በማለት ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
"ወረርሽኙ ከጀመረው ወር ሞልቶታል፣ ከዚህ በፊት ከአንድ ሁለት አመት ጀምሮ ለተከታታይ አመታት የወባ ወረርሽኝ በአካባቢው ተከስቶ ጊዚያዊ መፍትሔ እንጂ በዘላቂነት የወባ ወረርሽኑን ለማጥፋት ዞኑም ሆነ ክልሉ ትኩረት አርገው አልሰሩበትም። አሁን ተመልሶ መጥቷል" በማለት አስረድተዋል።
አንድ የህክምና ባለሙያ "የሞት ቁጥር ይሄን ያህል ነው ብዬ ለመግለፅ ባልችልም ሰው ሳይሞት እና ሳይቀበርበት የሚቀር ቀን የለም። በጣም የሚያሳዝነው በወረዳው አንድ ጤና ጣቢያ ብቻ ያለን ሲሆን በቂ የሰው ሀይል እና የመመርመርያ መሣርያ እንዲሁም በቂ የመድሃኒት አቅርቦት እንኳን የለውም" ብለው ለሚድያችን ተናግረዋል።
አክለውም "ወረፋ የደረሰው በዚች አንድ ጤና ጣቢያ ይታከመል፣ ያልደረሰው ደግሞ ሳይታከም ይሄዳል። ጤና ጣቢያው መሸከም ከሚገባው በላይ ሕዝብ እያስተናገደ ነው፣ ወረርሽኙን ቶሎ ለማስቆም ርብርብ ካልተደረገ ከዚህም የከፋ ጉዳት ያስከትላል" ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር በ2002 ባወጣው የጤና ስርዓት እርከኖች መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ወይም የዲስትሪክት ጤና ስርዓት ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ ህዝብ፣ በገጠር ጤና ጣቢያ ከ15 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሕዝብ፣ በከተማ ጤና ጣቢያ 40,000 ሕዝብ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ60 ሺህ እስከ 100,000 ሕዝብ ያገለግላል ይላል።
"ስለዚህ ከ80 ሺህ በላይ ህዝብ ብዛት ልክ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ የከተማ የጤና ማዕከል እና የገጠር ጤና ጣብያ ያስፈልጋል። በተለይ ለወባ ተጋላጭ አካባቢ ስለሆነ ይህ በፍጥነት ያስፈልጋል" የሚሉት ነዋሪዎቹ ናቸው።
"በዳውሮ ዞን ጌና ወረዳ ወልድሃኔ ጤና ጣቢያ በወባ ወረርሽኝና በመሰል በሽታ የሰው ህይወት እንደ ቅጠል እየረገፈ ነው ያለው። በጣም የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ በወረዳ ውስጥ ያሉ ከ14ቱ ቀበሌዎች በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል (ኦሞ ናዳ ቀበሌ) የሚገለገልበት ተቋም ቢሆንም በቂ ተኝተው የመታመከምያ ቦታ ባለመኖሩ ሰው ሜዳ ላይ ተኝቶ እየታከመ ነው" የሚሉት የጤና ባለሙያው ሁኔታው አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ብለዋል።
የዳውሮ ዞን እስካሁን በጉዳዩ ዙርያ የሰጠው ቀጥተኛ ምላሽ ባይኖርም የጤና ተቋማት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተገቢ የሆነ የድጋፍና ክትትል ሥራ ወሳኝ እንደሆነ ከሁለት ቀን በፊት በኮሚኒኬሽን ገፁ በኩል አስታውቆ ነበር።
-መሠረት ሚድያ-




