(መሠረት ሚድያ)- በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው ከሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መሀል አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 300 የፖለቲካ እስረኞች የተሀድሶ ስልጠና አጠናቀው ዛሬ ምሽት ወይም ነገ ከእስር እንደሚፈቱ መሠረት ሚድያ አረጋግጧል።
ስልጠናው ያተኮረው ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መስራት ስለሚቻልበት ሁኔታና ሰላምን እንዴት ማጽናት ይገባል በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ መላኩ ፋንታ፣ እንዲሁም ከሰላም ሚኒስቴርና ከፍትሕ ሚኒስቴር የተውጣጡ አመራሮች መሆናቸው ታውቋል።
የይቅርታ ሰነድ የፈረሙት እስረኞቹ የተሐድሶ ስልጠናውን ዛሬ ያጠናቀቁ ሲሆን ዛሬ ምሽት ወይም ነገ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
ይህንን የተሐድሶ ስልጠና አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ማዕረጉ ቢያበይንና አቶ ከፋለ እሱባለውን ጨምሮ 300 የአማራ የፖለቲካ እስረኞች ወስደዋል።
ከነዚህ የአማራ የፖለቲካ እስረኞች ጋር በኦሮሚያ ክልል በ2013 ዓ.ም በጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃና ከዚያ ወዲህ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎችም በጋራ ስልጠናውን መካፈላቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር ምንጮች አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አሸማጋይነት በአማራ ክልል ለደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ኃላፊነት እወስዳለሁ፣ ጥፋትም አጥፍቻለሁ፣ በዚህም ተጸጽቻለሁ፣ ወደፊትም የመንግሥት የሰላም ዘብ ለመሆን ቃል እገባለሁ የሚልና በአማራ ክልል ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ ታጣቂ ኃይል አውግዘው እንዲፈርሙ ኮሚሽኑ ሲያግባባ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት እስረኞቹ ይቅርታ የጠየቁ (የፈረሙ) እና ይቅርታ ያልጠየቁ (ያልፈረሙ) በሚል በሁለት ተከፍለው ቆይዋል።
የተሐድሶ ስልጠናውን የወሰዱትም አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ 300 እስረኞች ናቸው። በዚህ መሠረት ይቅርታ ያልጠየቁ ወይም ያልፈረሙ 30 የፖለቲካ እስረኞች አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም ፣ ጋዜጠኛ መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ፣ ጋዜጠኛ ዓባይ ዘውዱን ጨምሮ 30 የፖለቲካ እስረኞች ይቅርታ ባለመጠየቃቸው የተሐድሶ ስልጠና አልወሰዱም፣ ከእስርም እንደማይፈቱም ታውቋል።
ከእስር የሚፈቱት እስረኞችን ጉዳይ ለመዘገብ የመንግስት ሚድያዎች ሰፊ ዝግጅት እያረጉ መሆኑም ታውቋል።
| መሠረት ሚድያ |



ያልተፈቱትን:- የመድሐኒዓለም ያውቃል ኑረን ምን ጠቀምን። እኛ ወዮ ለአራጆች
እነዚህ የሕሊና እስረኞች ወደ ቤተሰቦቻቸው
ፈጣሪ በሰላም ይቀላቅላቸው
አንፈርምም ያሉት የሕሊና እስረኞች የምርጥ
ሕሊና ባለቤቶች ናቸው ለእነሱም
የአለማቱ ንጉስ ፈጣሪያችን ፍትሕን ይስጣቸው
የገዥው ፓርቲ እድሜ ግን ነቅዟል
የመንግስት ሚዲያ የተባሉት
የገዥው ፓርቲ ሚዲያዎች በሚል ይስተካከል