ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ጂንካ አካባቢ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል 300 ሺህ ዶላር በአለም ጤና ድርጅት አስቸኳይ ፈንድ በኩል መልቀቃቸውን ገለፁ
(መሠረት ሚድያ)- ጂንካ ከተማ ውስጥ ባለፉት ሶስት እና አራት ቀናት ውስጥ በተከሰተ አጣዳፊ በሽታ ምክንያት ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ሚድያችን ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስቴር በሽታው ሄሞራጂክ ፌቨር (hemorrhagic fever) እንደሆነ እንደተጠረጠረ ገልፆ ተጨማሪ ምርመራ እያረገ መሆኑን ገልፆ ነበር።
በዛሬው ዕለት የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ወረርሽኙን ለመከላከል ድርጅታቸው 300 ሺህ ዶላር በአለም ጤና ድርጅት አስቸኳይ ፈንድ በኩል መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የአለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ቴድሮስ ወደተጠቁት አካባቢዎች ባለሙያዎች፣ መድሀኒቶች እና ሰውነት መከላከያ ቁሳቁሶች መላካቸውን ጠቅሰዋል።
"የአለም ጤና ድርጅት የተጠቁ ሰዎችን ልየታ ለማድረግ ድጋፍ ያደርጋል፣ ናሙናዎች ለተጨማሪ ምርመራ ተልከዋል። ከአለም ጤና ድርጅት አስቸኳይ መጠባበቂያ ላይ 300 ሺህ ዶላር እንዲለቀቅ ተደርጓል" ብለዋል።
በተጨማሪም በሽታው ወደሌሎች ሀገራት እንዳይተላለፍ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ቢሮዎች በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ የጤና ሀላፊዎች በፍጥነት በበሽታው ዙርያ መረጃ ማጋራታቸውን አሞግሰዋል።
መላ የጂንካ ከተማን ህዝብ ባስደነገጠው ክስተት የጂንካ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም አንድ ዶክተር እና አንድ ነርስ በበሽታው ከተጠቁ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።
አንድ ስሜ አይጠቀስ ያለ በጂንካ ሆስፒታል የሚሰራ የጤና ባለሙያ ክስተቱ ትክክል መሆኑን በመግለፅ አሁን ላይ ሶስት ታማሚ በሆስፒታሉ እንዳለ እና ከታማሚዎቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በርካቶች እንዳሉ ትናንት ለሚድያችን ተናግሮ ነበር።
"ሁሉም የሞቱት መጀመሪያ ከሞተው ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው፣ እንዲሁም በሁሉም ላይ አንድ አይነት ምልክቶች ታይተዋል፣ እና በሽታው ከሶስት እስከ አምስት ቀን ባለው ግዜ ለሞት የሚዳርግ ነው" ያሉት የጤና ባለሙያው ይህ ሁሉም በፍርሀት እንዲዋጥ አርጓል ይላሉ።
ህይወታቸው ያለፉት ሰዎች በአፋቸውና በአፍንጫቸው ደም እየፈሰሰ እንደነበር ታውቋል። የጤና ሚኒስቴር በሽታው ሄሞራጂክ ፌቨር (hemorrhagic fever) እንደሆነ የተጠረጠረ ገልፆ ስምንት ሰዎች መጠቃታቸውን ከመግለፅ ውጭ ህይወታቸው ስላለፉት ስድስት ሰዎች ያለው ነገር የለም።
-መሠረት ሚድያ-



