መሠረት ሚድያ ከአራት ቀን በፊት ያወጣውን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ ኢሚግሬሽን አዲስ አሰራር ጀመረ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን ከአራት ቀን በፊት በአዲስ አበባ ባለው ዋናው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በአንዳንድ የተቋሙ ሰራተኞች እየተፈፀመ ያለውን የሙስና አሰራር ማጋለጡን ተከትሎ ተቋሙ ለአስቸኳይ ፓስፖርት አመልካቾች አዲስ አሰራር ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት በኦንላይን ብቻ የነበረውን የአዲስ አስቸኳይ ፓስፖርት አገልግሎት በአካልም እንዲሆን ተወስኗል።
"ከግንቦት 04/09/2017 ዓ.ም ጀምሮ አስፈላጊ ሰነዶችን በመያዝ ጥቁር አንበሳ በሚገኘው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መ/ቤት በአካል በመምጣት መስተናገድ የምትችሉ መሆኑን በአክብሮት እናሳውቃለን" በማለት ተቋሙ ዛሬ አሳውቋል።
መሠረት ሚድያ ከቀናት በፊት ባወጣው የምርመራ ዘገባው የተወሰኑ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞችና ደላሎች ተመሳጥረው ለአስቸኳይ ፓስፖርት ከፍተኛ ገንዘብ በሲስተም አድሚኖች በኩል እየተቀበሉ ቀጠሮ እንደሚያስይዙ አጋልጦ ነበር።
ተቋሙ በቅርቡ ለ 2 ቀን ቀጠሮ 25 ሺ ብር፣ ለአምስት ቀን ቀጠሮ 20 ሺ ብር በማስከፈል በኦንላይን በሚሞላ ፎርም አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ተቋሙ ሲስተሙ ይሰራል በማለት ለህዝብ ቢያሳውቅም ኦንላይን የሚሞላው ፎርም ግን በማንኛውም ጊዜ ሲከፈት 'There is no available appointment date, Please check Later!' የሚል ጽሁፍ እያመጣ እየሰራ እንዳልሆነ ማንም ማረጋገጥ የሚችለው ሀቅ ነው፣ ይህ ደግሞ ለወራት የዘለቀ ችግር እንደሆነ ይታወቃል።
አሁን ላይ ከተቋሙ ግቢ ውጪ ያሉ አካላት እና የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ተመሳጥረው ለአስቸኳይ ፓስፖርት እስከ 35 ሺህ ብር እያስከፈሉ ሲሆን በተቋሙ ውስጥ ከሚሰሩ አንዳንድ የአይቲ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ አመራሮች የሚሳተፉበት ኔትወርክ በመዘርጋት ሲስተሙን ከእነርሱ ጋር ተመሳጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች ብቻ ማግኘት እንዲያደርጉ በማመቻቸት ዜጎችን እየበዘበዙ እንደሚገኙ ዘግበን ነበር።
አስቸኳይ ቀጠሮ የሚባለው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተዘግቶ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች የሆኑ የተቋሙን ሲስተም አድሚን (admin) የሚቆጣጠሩ ሰራተኞች በውስጥ መስመር ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ህዝቡን 35,000 ከተቀበሉ በኋላ እነዚህ አድሚኖች ከ5,000 ብር እስከ 6,500 ብር እንደሚቀበሉ መረጃ አጋርተን ነበር።
የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መረጃ ግን የኦንላይን ሲስተም አልሰራ ያላቸው በአካል ቀርበው መስተናገድ እንደሚችሉ ነው።
መረጃን ከመሠረት!





ስለመረጃው ልባዊ ምስጋናየ ነው