ሚድያችን በቅርቡ በምርመራ ዘገባው በዳሰሰው የኦንላይን ቤቲንግ ዙርያ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በበርካታ ከተሞች ታግዷል የተባለው ቤቲንግ በኦንላይን ተባብሶ መቀጠሉን ሰፋ ባለ የምርመራ ዘገባችን መስከረም 4/2018 ዓ.ም መዳሰሳችን ይታወሳል (https://tinyurl.com/4s6szcbn)
ለዚህ የኦንላይን ቤቲንግ መስፋፋት ደግሞ በዲጂታል መልኩ በሚፈፀም ክፍያ (deposit) እና የአንዳንድ የብሔራዊ ሎተሪ ሰራተኞች ድርጊቱ ላይ መሳተፍ ምክንያት መሆኑን ጠቁመን ነበር።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ዛሬ ምሽት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።
ተቋሙ ይፋ እንዳደረገው በቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶችና ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር በሚባሉ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተባባሪ ተቋማት ዙሪያ ጥናትና ክትትል ሲከናወን ቆይቷል ብሏል።
አክሎም ፈቃድ ያላቸውና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በገቡት ውል መሰረት የማይሠሩ፣ በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው በመገኘታቸው ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው እንዲሁም ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በስፖርት አወራራጅነት ተሰማርተው የነበሩ አካላት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ትስስር አማካይነት በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው ተገኝተዋል ብሏል።
"የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ትብብር አማካኝነት 24 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል" በማለት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በተለይ በሕጋዊነት ሽፋን ፈቃድ ያወጡት ድርጅቶች ላይ ክትትል ለማድረግ ሙከራ በተደረገበት ወቅት ሁሉም ፈቃድ ሲያወጡ ይዘውት ከነበረው ቢሮ መልቀቃቸውና አድራሻቸውን መሰወራቸው ተረጋግጧል ተብሏል።
የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ስርዓቶችን ከሚያሳልጡላቸው የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር በአጠቃላይ ሲያንቀሳቅሱት ከነበረው የገንዘብ መጠን መንግሥት በተለያዩ የገቢ አማራጮች ማግኘት የነበረበትን 100 ቢልዮን ብር በላይ መሰወራቸው እንደተደረሰበት አመልክቷል፡፡
የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ በተለያዩ የገንዘብ ክፍያ ስርዓቶች አማካይነት የሚሰበስቡትንና የሚያዘዋውሩትን የገንዘብ መጠን ያማከለ ግብር አለመክፈላቸው እንደተደረሰበት የጠቆመው የደህንነት ተቋሙ በክሪፕቶከረንሲ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ገንዘብ ማስተላላፊያ አማራጮች አማካኝነት የሚያገኙትን ገቢ በውጭ ምንዛሪ በመቀየር ሲሰውሩና ከሀገር እንዲወጣ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ "ከእዚህ በኋላ በከተማው የቤቲንግ ወይም የስፖርት ውርርድ ቤት አይኖርም" ብሎ ያስታወቀው ልክ የዓመት ገደማ ነበር። የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት በከተማዋ የሚገኙ 4,118 የቤቲንግ ቤቶችን ዘግተናል፣ ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የውርርድ ወይም ቁማር ቤት አይኖርም ብለውም ነበር።
"ልጆቻችን አዕምሯቸው በቁማር ምክንያት እየተበላሸ ነው፣ እቃም ጭምር ከቤት እየተሰረቀ እየተሸጠ ነው። ለትዳር ፍቺ ጭምር መነሻ ሆኗል እየተባለ ቅሬታ ሲነሳ ነበር፤ ምላሽ ተሰጥቶታል" ያሉት ሀላፊው በዘርፉ ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ ሌላ ስራ ቀይረው እንዲሰሩ ትዕዛዝ ተላልፏል ብለዋል።
ይሁንና መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ ለበርካታ ቀናት ሲያደርግ የነበረው ክትትል እንደሚያሳየው ቤቲንግ በቴሌ ብር እና በሌሎች የዲጂታል አማራጮች በሚፈፀም ክፍያ (deposit) እየታገዘ በተለይ በኦንላይን ተስፋፍቶ ቀጥሏል።
ክልከላው እስካሁን ያልተነሳ ቢሆንም አሁን ላይ በሀገሪቱ ውስጥ በጣም ብዙ የሚባሉ አቋማሪ ድርጅቶች በግልፅ በኦንላይን ስራ እየሰሩ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
"ብሔራዊ ሎተሪ የሚቆረጠውን እየቆረጠ፣ ድርጅቶቹ ደግሞ በውስጥ በኩል በድብቅ እያጫወቱ ነው። የሚገርመው ደግሞ የሚጠይቃቸው አካል ስለሌለ ብሩን ገቢ/ዲፖዚት ስታረግ እንደልብ ይገባል" የሚሉት አንድ የብሔራዊ ሎተሪ ምንጫችን ናቸው። አክለውም አቋማሪ ድርጅቶቹ ከአንዳንድ የብሔራዊ ሎተሪ ሰዎች ጋር በመመሳጠር እየሰሩ ይገኛሉ ይላሉ።
በተለይ ዳሼ ቤቲንግ፣ ቫሞስ ቤቲንግ እና ሁሉ ስፖርት የሚባሉ ድርጅቶች እዚህ ስራ ላይ በስፋት ተሰማርተው እንደሚገኙ አስረድተዋል። እነዚህ ለምሳሌ ቀረቡ እንጂ ተመሳሳይ ድርጊት ላይ የተሰማሩት ከ20 በላይ ናቸው ተብሏል።
"ድርጅቶቹ ኮል ሴንተር ብቻ ነው ያላቸው፣ ቢሮአቸውን አይናገሩም። በስልክ ብቻ ነዉ የሚገኙት፣ በጣም ብዙ ሰው በዚህ ነገር ንብረቱን መኪናውን ያጣ አለ" የሚሉት ደግሞ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሌላ ግለሰብ ናቸው። ይህን ተከትሎ ቤቲንግን ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በከለከሉት እንደ ሀዋሳ እና መቐለ ባሉ ከተሞች ቤቲንግ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
"መንግስት ያወጣውን ክልከላ ማስፈፀም አልቻለም፣ ያውም ትውልድ ገዳይ የሆነን ቤቲንግ የሚባል መጥፎ መርገምትን። እንደ እኔ በርካቶች ሜዳ ላይ ቀርተዋል፣ በሚድያ አይነገርም እንጂ ራሳቸውን የሚያጠፉም ብዙ ናቸው። ከዚህ በላይ አስቸኳይ ነገር ያለ አይመስለኝም" በሚል ለሚድያችን ቃላቸውን የሰጡት ሌላኛው የቀድሞ የቤቲንግ ተጠቃሚ ናቸው።
በኦንላይን የሚፈፀሙ ውርርዶችን መንግስት በቀላሉ መዝጋት ይችላል የሚሉት ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የአይቲ ባለሙያ ናቸው።
"ውርርዶቹ የሚከናወኑበትን አድራሻ መዝጋት ይቻላል፣ በቴሌ ብር የሚከናወኑ ክፍያዎችንም የድርጅቶቹን ቁጥር ተከታትሎ በመለየት ማገድ ይቻላል። ቴክኖሎጂው ይህን ማድረግ ይፈቅዳል" በማለት አስረድተዋል።
-መሠረት ሚድያ-





እኔም እኮ መረጃ ነበረኝ እንዴት እንደማገኛችሁ አላውቅም ከቻላችሁ ብታገኙኝ