ወልዲያ ከተማ ውስጥ ከቤተክርስቲያኖች ውስጥ ተይዘው የተወሰዱ የዓብነት ተማሪዎች ተለቀቁ
(መሠረት ሚድያ)- በርካታ የዓብነት ተማሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወልዲያ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ቤተክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ውስጥ ታፍሰው መወሰዳቸውን ባሳለፍነው ሰኞ ህዳር 22/2018 ዓ.ም መረጃ አጋርተን ነበር።
ስልካቸውን ከተቀሙ በኋላ በሚሊሻዎች የተወሰዱት የዓብነት (የቤተክርስቲያን) ተማሪዎቹ በወልዲያ ከተማ የሚገኘው የቲንፋዝ ደብረ በረከት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርሰቲያን እና የሌሎች ቤተክርስቲያኖች ተማሪዎች መሆናቸውን ዘግበን ነበር።
"ቤተ ክርስቲያኒቱ ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ በደብዳቤ ብትጠይቅም እስካሁን ምላሽ አልተገኝም። አፍነው የወሰዱት የሚሊሻ አባላቱ በወሰዱት በእያንዳንዱ ተማሪ 7 ሺህ ብር እየጠየቁ ይገኛሉ" በማለት አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ እና ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጫችን ለመሠረት ሚድያ ተናግረው ነበር።
የተወሰዱት ተማሪዎች ከቲንፋዝ ደብረ በረከት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሶስት፣ ከፒያሳ መንበረ ንግስት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ደብር አምስት፣ ከተማው ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ደብር የሚማሩ አስራ አምስት ነበሩ።
አሁን የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው ሚድያችን መረጃውን ማውጣቱን ተከትሎ የመንግስት ሀላፊዎች ጣልቃ በመግባት ተማሪዎቹ ካለ ክፍያ እንዲለቀቁ ማድረጋቸው ታውቋል።
"ተይዘው የነበሩ ተማሪዎች ያለምንም ክፍያ ተፈትትዋል" በማለት አንድ ምንጫችን ዛሬ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ይህ ሊሆን የቻለውም መረጃው በሚድያ መውጣቱን ተከትሎ ብዙ ውዝግብ ካስነሳ በኋላ የክልሉ ባለስልጣናት በቀጥታ በሰጡት ትዕዛዝ ካለምንም ክፍያ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን በሚሊሻዎች አሰራር ዙርያ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል።
-መሠረት ሚድያ-



