በአዲስ አበባ ያሉ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች የመራጮችን ሚስጥራዊ መረጃ በግዴታ አሳልፈው እንዲሰጡ በወረዳ አመራሮች ጥያቄ እየቀረበላቸው መሆኑን ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች በምርጫ ክልል ኃላፊዎች እና በወረዳ አመራሮች አማካኝነት ከፍተኛ እንግልት እና ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን ለሚድያችን ተናገሩ።
አስፈፃሚዎቹ በላኩልን ዝርዝር መረጃ መሰረት በገለልተኝነት እንዲያገለግሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰለጠኑ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን "ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ወረደ" በተባለ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የመራጮችን ሚስጥራዊ መረጃ አሳልፈው እንዲሰጡ በወረዳ አመራሮች ጥያቄ ሲቀርብላቸው ቆይቷል።
ይህ ድርጊት የተጀመረው የወረዳ አመራሮች ቀደም ብሎ ቤት ለቤት በመዞር የመዘገቡት የመራጮች መረጃ በኦንላይን ከተመዘገበው መረጃ ጋር ባለመጣጣሙ እና የበርካታ መራጮችን ሙሉ መረጃ ማግኘት ባለመቻላቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።
የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎቹ ይህንን ሕገ-ወጥ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የታማኝነት ቃላቸውን ለመጠበቅ ቢሞክሩም የየምርጫ ክልሉ ኃላፊዎች ከመንግሥት አመራሮች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ለጣቢያ አስፈፃሚዎች የተሰጠውን የኢሜል አድራሻ እና የይለፍ ቃል (Password) አሳልፈው መስጠታቸው ታውቋል።
በዚህም ምክንያት የወረዳ አመራሮች ለምዝገባ ተብሎ ከፕሌይ ስቶር የወረደውን አፕሊኬሽን በመጠቀም የመራጮችን ሙሉ ስም፣ ስልክ ቁጥር እና የመራጭነት መታወቂያ (Voter ID) ያለምንም ከልካይ እየወሰዱ መሆኑ ተረጋግጧል።
“በዜጎች የግል መረጃ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል”
ይህ ተግባር የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በላይ በዜጎች የግል መረጃ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።
አስፈፃሚዎቹ አክለው እንደገለጹት በኦንላይን የምዝገባ ሂደት ወቅት በአፕሊኬሽኑ ላይ የሚታዩ ስህተቶችን እና ጉድለቶችን በተደጋጋሚ ለበላይ ኃላፊዎች ቢያሳውቁም ምንም ዓይነት ማስተካከያ ሳይደረግ እስከ ምርጫው ዋዜማ መድረሱ አጠራጣሪ ነው።
በአሁኑ ወቅት የሕዝብን አደራ ለመጠበቅ የሚጥሩ አስፈፃሚዎች በወረዳ አመራሮች "ጥርስ እየተነከሰባቸው" እና የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እየደረሱባቸው በመሆኑ ለደህንነታቸው ዋስትና እንደሌላቸው ገልጸዋል።
በምርጫ ክልል ኃላፊዎች እና በፖለቲካ አመራሮች መካከል ያለው ይህ የጥቅም ትስስር የምርጫውን ነፃነትና ፍትሃዊነት ክፉኛ እያበላሸው መሆኑን የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሚደርስባቸው ማንኛውም ጥቃት ተጠያቂው ማን እንደሆነና በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ ውጤቱ ምን ያህል ተአማኒ ይሆናል የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።
| መሠረት ሚድያ |


