ጋዜጠኞቹ ቀይ ቦኔት ባደረጉ እና ጭምብል ባጠለቁ አካላት ታግተው ከተወሰዱ በኋላ ደብዛቸው እንደጠፋ ይገኛል
(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት እውቅ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በሀይል ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ደብዛቸው ጠፍቷል፣ ድርጊቱም እየተባባሰ የመጣውን ዜጎችን በሀይል ይዞ የመሰወር ድርጊት አመላካች ነው ተብሏል።
የመጀመርያው ታጋች ነሀሴ 5/2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ጭምብል ባጠለቁ አካላት ታግቶ የተወሰደው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሀመድ ነው።
አብዱልሰመድ በበርካቶች በልዩ ድምፁ በሬድዮ የሚያውቁት ሲሆን አሁን ላይ በሰለንዳ ኤቨንትስ እና ኮሚኒኬሽን እየተዘጋጀ በሚቀርበው 'ቅዳሜ ገበያ' ፕሬግራም ላይ ተባባሪ አቅራቢ ነበር።
ሰለንዳ በጉዳዩ ዙርያ ባወጣው መግለጫ አብዱልሰመድ እስካሁን የት እንደሚገኝ እንደማይታወቅ ገልጾ ይህም ቤተሰቡን ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ እንደከተተ ጨምሮ አስታውቋል።
"ባለፉት ቀናት የጓደኛችንን በህይወት መኖር እና የት እንደሚገኝ ለማወቅ ቤተሰቡ በሚያደርገው ጥረት የራሳችንን ጥረት ያደረግን ሲሆን ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ግን እስካሁን የተጨበጠ መረጃ ማግኘት አልተቻለም" በማለት ሰለንዳ አስታውቋል።
አብዱልሰመድ በቅርቡ ቤተሰቡን የተቀላቀለውን ህፃን ጨምሮ የአራት ልጆች አባት ሲሆን በጋዜጠኝነት ሙያ ወደ 30 ለሚጠጋ አመታት ሰርቷል።
በሌላ በኩል ለበርካታ አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገለው ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ በተመሳሳይ ሀሙስ እለት መኖርያ ቤቱ አቅራቢያ ቀይ ቦኔት በለበሱ የፀጥታ አካላት ታግቶ መወሰዱን የመሠረት ሚድያ ምንጮች ጠቁመዋል።
ሪፖርተር ጋዜጣ በባልደረባው እገታ ዙርያ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛ ዮናስ ላለፉት አምስት ቀናት ማለትም ከነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ባለመግባቱ በእጅ ስልኩ ላይ ቢደወልለትም ሆነ ከቤተሰቦቹ ለማጣራት ቢሞከርም ማግኘት አልተቻለም።
"በሥራ ላይ እያለ የገባበት በመጥፋቱ የሥራ ባልደረቦቹም ሆኑ የሚቀርቡት ጓደኞቹ በእጅ ስልኩ ላይ ቢደውሉም ማግኘት አልተቻለም" ያለው ሪፖርተር ጋዜጠኛ ዮናስ በሚኖርበት በሸገር ከተማ ኮዬ ፌጬ ኮንዶሚኒዬም በመሄድ በተደረገ ማጣራት ተይዞ የተወሰደው ረቡዕ ምሽት ፊታቸውን በጭምብል በሸፈኑ ሰዎች መሆኑን ባካባቢው ካሉ የጥበቃ ሠራተኞች ለማወቅ ተችሏል ብሏል።
ከሁለቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪ 'Salon Tube' የተባለ የዩትዩብ ቻናል ባለቤት የሆነው ሀሰን ሰይድ በተመሳሳይ ሀሙስ እለት ተይዞ መወሰዱ ታውቋል።
ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ እና ጋዜጠኛ ዮናስ Salon Tube ላይ በፍሪላንስ አልፎ አልፎ እንደሚሰሩ ሚድያችን የሰማ ሲሆን እገታው ግን ከዚህ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ እስካሁን አልታወቀም።
በሁለቱ ጋዜጠኞች እገታ ዙርያ በመንግስት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድኖች በጋዜጠኞቹ መታሰር ዙርያ በመጪው ሳምንት መግለጫ እንደሚያወጡ ታውቋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጋዜጠኞቹ እገታ ዙርያ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ያለአግባብ ያሠርኩት ጋዜጠኛም ሆነ ዜጋ የለም የሚል ምላሽ ሲሰጥም ተመልክተናል ብሏል።
"የዚህ ምላሽ አሳሳቢነት አንድም መንግሥት ድርጊቱን እየፈፀመ ነገር ግን እየደበቀው ከሆነ መንግሥት ሕገወጥ ተግባራትን ሆነ ብሎ እየፈፀመ ነው የሚያስብል ሲሆን በሌላ መልኩ እነዚህ ተግባራት የሚፈፀሙት ከመንግሥት እውቅና ውጪ በሌሎች በተደራጁ አካላት ከሆነ መንግሥት በቅጡ የሀገሪቱን ፀጥታ እና የዜጎችን ደኽንነት እያስጠበቀ አይደለም የሚል ስጋት ዜጎች ላይ እንዲፈጠር ያደርጋል" ብሏል።
አክሎም "እነዚህ ሁነቶች በዋነኝነት የሚያመሩት ዜጎች ጠባቂ የለኝም ከሚል ስጋት በገዛ እጃቸው ደኽንነታቸውን ለማስከበር መሞከር ሲሆን በተጨማሪም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚፈታተኑ ሕገወጦች እንዲበራከቱ በማድረግ የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ እና የዜጎች ደኽንነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚከት አስፈሪ ሁነት ነው" በማለት አቋሙን አስፍሯል።
*መሠረት ሚድያ*



