ከፍተኛ የክልል ባለስልጣናት የሚሳተፉበት እና አንድ ሊትር ናፍጣ ማደያ ውስጥ እስከ 280 ብር የሚሸጥበት የጋምቤላ ክልል
(መሠረት ሚድያ)- ባለፉት ጥቂት ወራት፣ በተለይ ደግሞ የብር መዳከምን ተከትሎ የነዳጅ እጥረት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ተባብሶ መቀጠሉ ይሰማል።
መንግስት 'ስግብግብ' የሚላቸውን ነጋዴዎች እና ነዳጅ አከፋፋዮች ደጋግሞ ሲወቅስ ቢሰማም በአንዳንድ ስፍራዎች ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ጭምር የሚሳተፉበት ህገወጥ ድርጊት መሆኑን መሠረት ሚድያ ከዚህ በፊት ሀዋሳን ምሳሌ በማድረግ መዘገቡ ይታወሳል።
የዛሬው ዘገባችን ደግሞ ወደ ጋምቤላ ክልል ይወስደናል።
ጋምቤላ ውስጥ እንደ የወርቅ ማዕድን ፍለጋ ያሉ ስራዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸው በርካታ ዜጎች ወደ ክልሉ ስራ ለመስራት በብዛት እየሄዱ ይገኛሉ።
ይሁንና ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ አሻጥር ከክልሉ የንግድ ቢሮ ጀምሮ እስከ የክልሉ ፕሬዝዳንት በሚሳተፉበት መልኩ መጀመሩን የደረሱን ጥቆማዎች እና ማስረጃዎች ያሳያሉ።
"አንድ ሊትር ናፍጣ ከ220 ብር እስከ 280 ብር በነዳጅ ማደያ ውስጥ እየተሸጠ ነው። ለምሳሌ እኔ ለሳይቴ የሚሆን 50 በርሜል (10ሺ ሊትር) ከክልሉ ንግድ ቢሮ በፍቃዴ አስፈቅዳለሁ። እነሱም ፈቃዴን አይተው ለአንዱ ማደያ እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይፅፉልኛል። ከዛ የማደያው ባለቤቶች ከአዲስ አበባ ነዳጅ አልመጣም ወረፋ ያዝ ትባላለህ" በማለት ጉዳዩን ያስረዱት አንድ በክልሉ ለስራ የሄዱ ግለሰብ ናቸው።
"በዚህ መሃል ደላሎች ይመጡና ነዳጅ አለ፣ ሌሊት ይቀዳልሃል በ280 ብር ትገዛለህ ወይ? ትባላለህ። እሺ ብለህ ከተደራደርክ በኋላ ገንዘቡን ወደ ባለማደያ አካውንት ውስጥ እንድታስገባ ካደረጉህ በኋላ ሌሊት ይቀዳልሃል" በማለት ጨምሮ አስረድቷል።
ሌላኛው ጥቆማ ሰጩ ደግሞ "ይህ ነገር ሲደረግ ከክልሉ ንግድ ቢሮ ሃላፊዎች ጀምሮ እስከ ፕሬዝዳንቷ ቢሮ ድረስ የጥቅም ተካፋይ ስለሆኑ ያውቁታል። የአንድ ሊትር ናፍጣ ዋጋ በህጋዊ መንገድ 125 ብር የነበረ ሲሆን አሁን እጥፍ ሆኗል። እዚህ አገር በሰማያዊ በርሜሎች ሲኖትራክ ላይ ጭነህ ነው ናፍጣ የሚቀዳው" በማለት የበኩሉን አስተያየት ሰጥቷል።
ሚድያችን የደረሰው ጥቆማ እንደሚያሳየው በዚህ መልኩ በሚሰራ ህገወጥ ስራ ከአንድ መኪና እስከ አንድ ሚሊየን ብር ትርፍ ያገኙበታል።
"ብዙ ባለ ሳይቶች እኛን ጨምሮ ስራ አቁመናል። አንዳንዱ የቤቱን ካርታ አስይዞ ሊሰራ የመጣ ነው። ማሽን ተከራይቶ የማሽን ሂሳብ እየቆጠረብን ነው። ከስር በየማደያው በርሜል ጭነው የቆሙ መኪኖች ግን በየቦታው ይታያሉ" በማለት ማስረጃቸውን አቅርበዋል።
በዚህ ዙርያ የጋምቤላ ክልል ንግድ ቢሮን መረጃ ለመጠየቅ ከዓርብ እለት ጀምሮ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
መረጃን ከመሠረት!



