አብሮነት-ኢትዮጵያ በበይነ መረብ የሚያካሂደው ህዝባዊ ውይይት ከመጀመሩ በፊት ዩትዩብ በመላው ኢትዮጵያ ታገደ
(መሠረት ሚድያ)- 'ጦርነት ይቁም! ሰላም ይምጣ!' በሚል ርዕስ የመቶ ሺዎች የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ በበይነ-መረብ አደባባይ በዛሬው እለት ሊካሄድ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል።
ይሁንና ፕሮግራሙ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ዩትዩብ በመላው ኢትዮጵያ እንዳይሰራ መታገዱን መሠረት ሚድያ አረጋግጧል።
"በንጹሀን ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ የሚቃወምና በዓይነቱ የተለየ ታላቅ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ ለማካሄድ እየተዘጋጀን ነው" በማለት የአብሮነት-ኢትዮጵያ ለሚድያችን የላከው መግለጫ ይጠቁማል።
ትዕይንተ-ህዝቡ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 30 2017 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን የአጀንዳው የጋራ ባለቤትና ተባባሪ የመሆን ፍላጐት ባላቸው በርካታ መገናኛ ብዙሀን በመላው ዓለም ለሚገኘው ኢትዮጵያዊ በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል ተብሎ ነበር።
በዚህ ፕሮግራም ላይ በርካታ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚካሄዱ የተጠበቀ ቢሆንም መንግስት ሀገር ውስጥ ያሉ ተከታታዮች እንዳያዩት እንዳገደው ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።
መረጃን ከመሠረት!



