ቢቢሲ ላይ በመቅረብ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄዎች ያብራራችው ዶ/ር ማህሌት ጉዕሽ መታሰሯ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ እያካሄዱት ካለው የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው ሳምንት ግንቦት 6, 2017 ዓ/ም የቢቢሲ 'Focus on Africa' ፕሮግራም ላይ በመቅረብ ጥያቄዎቻቸውን ያብራራችው ዶ/ር ማህሌት ጉዕሽ መታሰሯ ታውቋል።
መሠረት ሚድያ እንዳረጋገጠው ማህሌት የተወሰደችው ከቤቷ ነበር፣ በዛሬው እለትም ከሌሎች በርካታ የጤና ባለሙያዎች ጋር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርባ እንደነበር ታውቋል፣ በነገው እለትም በድጋሜ እንደምትቀርብ ታውቋል።
ባለሙያዎቹ ያቀረቧቸው 12 ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ወደ ሙሉ የስራ ማቆም አድማ ከሰኞ ጀምሮ መጀመራቸው ይታወሳል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጤና ባለሙያዎች የዘገየ ቢሆንም መግለጫ እያወጡ ይገኛሉ።
ኢዜማ "አሁን ያለው እንቅስቃሴ ወደ ሀገራዊ ትርምስ እንዳንገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ደረጃ ላይ መገኘቱ አሳስቦናል" በማለት መብትን በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ መጠየቅን እደግፋለሁ ብሏል።
"ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግስት አካል ቀና ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በቸልተኝነት በማየት ተጨባጭ ያልሆነ ተስፋ ከመስጠት የዘለለ ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ መፍትሔ ሲሰጥ አልተስተዋለም" ያለው ኢዜማ ላለፈው አንድ ወር የጤና ባለሙያዎች ጥያቄያቸውን በፅሁፍ ጭምር እንዳሳወቁ እና መልስ እንዲሰጣቸው በአደባባይ እየጠየቁ የሚገኙ ቢሆንም መንግስት ለጉዳዩ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ በተቃራኒው እንቅስቃሴ ሲያደርግ መታየቱ አግባብነት ያለው ተግባር አይደለም ብሏል።
በሌላ በኩል መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ በጋራ በሰጡት መለጫ ከጤና ባለሙያዎች ጋር እልክ መጋባት መሞከርና ወደሌሎች አላስፈላጊ እርምጃዎች መግባት እጅጉን ያሳስበናል ብለዋል።
"የጤና ባለሙያዎቹን የዳቦ ጥያቄ ተከትሎ ባለን መረጃ በአንድ ሣምንት ውስጥ ከሰማንያ የሚበልጡ ሐኪሞች ለእሥር መዳረጋቸውን መረዳት ችለናል። ኢትዮጵያና መሰል የአፍሪካ ሀገራት ከደሃው በሚሰበሰብ ግብር በውድ ዋጋ ያስተማሯቸውን ሐኪሞች ወደ አደጉ ሀገራት እንዲፈልሱ በማድረግ (Brain Drain) የሚታወቁና የሚወቀሱ ሲኾን ይባስ ብሎ እጅግ አነስተኛና መሠረታዊ ለሚባል የዳቦ ጥያቄ ወደ ጅምላ እሥር መገባቱ ልብ ሰባሪ ነው" ብለዋል።
መረጃን ከመሠረት!




ያሳዝናል 😥