የመንግስት የፀጥታ አካላት ኦራል ተሽከርካሪ ጭምር እየተጠቀሙ በአስገራሚ ሁኔታ የሚሳተፉበት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር
ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለከፋ ህይወት፣ ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለሞት እየዳረገ እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል። መንግስትም ለችግሩ እልባት መፍትሄ እያፈላለገ እንደሆነ ይነገራል።
መሠረት ሚድያ ከሰሞኑ ሲያሰባስባቸው የነበሩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ የመንግስት የፀጥታ አካላት ራሳቸው በከፍተኛ ደረጃ እዚህ ድርጊት ላይ እየተሳተፉ እንደሆኑ ያሳያል።
"ከጎንደር- ዳንሻ- አብርጅራ- አብደረፊ- መተማ ያለው መስመር በከፍተኛ ደረጃ የሰዎች ዝውውር የሚካሄድበት ቦታ ሆኗል፣ እዚህ ላይ ደግሞ በግልፅ አንዳንድ ምግባረ ብልሹ የፀጥታ እና የደህንነት አመራሮች በቅንጅት እየሰሩ ወንጀሉን እየፈፀሙ ነው" የሚሉት አንድ የአካባቢው ነዋሪ በርካታ ከሀገር የሚሰደዱ ዜጎች በፀጥታ አካላት የኦራል መኪና ጭምር ሲጓጓዙ እንደሚታይ ያስረዳሉ።
"ይህ ነገር በጣም እየከፋ ነው። ዳንሻ ከተማ ውስጥ እንኳን በቅርቡ አንድ የትራፊክ ፖሊስ በባጃጅ ሰዎች ሊያሳልፍ ሲል በኬላ ጠባቂዎች ተይዟል" በማለት አስተያየት ሰጥቷል።
ዳሰሳችን እንደሚያሳየው በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ዋናው የህገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚጠቀሙበት የጎንደር- መተማ መንገድ ለተወሰነ ጊዜ በተዘጋበት ወቅት ጋብ ያለ ቢመስልም ሰሞኑን በመከፈቱ ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎች፣ የሰው አዘዋዋሪዎች፣ ሾፌሮች እና ለአንዳንድ በተግባሩ ውስጥ እጃቸው ላለ የመንግስት የፀጥታ አካላት ጥሩ የገቢ ማግኛ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
"የመንገዱ መከፈት ለማህበረሰቡ ጥሩ ቢሆንም ለነዚህ ወንጀለኞች ምላሽ እና ሰርግ ሆኖላቸዋል። ላለፉት 15 እና ከዚያ በላይ አመታት በዚህ ዙሪያ ብዙ ብዙ ተብሏል፣ ምንም ግን የመጣ ለውጥ የለም" ብለው ለሚድያችን የተናገሩት ደግሞ አንድ የመተማ ከተማ አካባቢ የመንግስት ሀላፊ ናቸው።
በየአመቱ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወደ ሊቢያ ይሻገራሉ የሚሉት እኚህ የመንግስት ሀላፊ በቅርቡ እንኳን የአንድ ምዕራብ ጎንደር ዞን መቀመጫ ከተማ የሆነችው የገንደ ውሃ ከተማ ወጣት በዚሁ መንገድ ወደ ውጭ እሻገራለሁ ብሎ ሊቢያ ላይ ህይወቱ አልፎ ለቤተሰቦቹ መርዶ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
"ለመሆኑ ማን ነው የሚያስቆመው? እኔ የመንግስት አካል ነኝ፣ ለእኔም እንቆቅልሽ ነዉ። ማህበረሰቡ በመድረክ ውይይት ላይ ሰው አዘዋዋሪው የመንግስት የፀጥታ አካል ነው ብሎ በግልፅ ነው የሚናገረው፣ ነገር ግን ምንም ለውጥ የለም" በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።
ይህ በመንግስት አካላት ጭምር የሚከናወን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደርሶ እና አዘዋዋሪዎቹ እጅ ከፍንጅ ተይዘው እንኳን ምንም የማፈረድባቸው መሆኑን ወይም ቢፈረድባቸው እንኳን ሊያሳምን የማይችል በመሆኑ አሁን አሁን ከነፃው ማህበረሰብ ውጪ ስለጉዳዩ የሚያስጨንቀው የመንግስት አካል አለ ብለው እንደማያስቡ እነዚህ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
"ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ወንጀሉ ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው መሆኑ ነው። እኔ 100 ፐርሰንት የማረጋግጠው በየኬላዉ ካለው የፀጥታ መዋቅር ጀምሮ እስከ ላይኛው አካል ድረስ በዚህ ትስስር መረብ እጃቸዉ ያለበት መሆኑን ነዉ" የሚሉት የመተማ አካባቢ የመንግስት ሰራተኛው ናቸው።
በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ በቅርቡ ለሪፖርተር ሲናገሩ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በኢትዮጵያ በተለይ በአራት መስመሮች ይደረጋል ብለው ነበር፣ በዋናነት በርካታ ዜጎች የሚወጡበት በር ደግሞ የምሥራቁ ነው ይላሉ።
"በዚህ መስመር በዓመት ከ150 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ወጣቶች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይሰደዳሉ፡፡ በርካታ ወጣቶች በደቡብ መስመርም ወደ ኬንያ በመውጣት መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደርጋሉ፡፡ በመተማ ሱዳን አድርገው ሊቢያን በመሻገር መዳረሻቸውን ጣሊያንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የሚያደርጉ ሲኖሩ፣ የሱማሌ ክልልም ሌላው የኢመደበኛ ስደት መስመር ነው" የሚሉት ሀላፊው ይህ ኢመደበኛ ስደት በርካታ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ ችግር አጋልጧል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የሰው አገር አቋርጠውና ድንበር ጥሰው ስለሚገቡ ለተለያዩ አደጋ እየተጋለጡ መሆናቸው በተደጋጋሚ በአለም አቀፍ ሚድያች ጭምር ይሰማል።
ከሚያጋጥማቸው ችግር በድንበር ጠባቂዎች የሚደርስባቸው ጉዳት ተጠቃሽ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጡ ያደርጓቸዋል፡፡ በተለይ ሴቶች ሲሆኑ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ለግዳጅ ሚስትነትና ለሴተኛ አዳሪነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ለጉልበት ብዝብዛም ይጋለጣሉ፡፡ በርካቶችም ለአካል ጉዳትና ሞት ይጋለጣሉ፡፡
መረጃን ከመሠረት!



