ዘንድሮ በአሜሪካ በሚካሄደው የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ፣ ሰይፉ ፋንታሁን እና ጆ ማሞ ተካተዋል
(መሠረት ሚድያ)- በሀገረ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የተመሰረተውና ለትርፍ ያልተቋቋመው ኖቫ ኮኔክሽን የሚያዘጋጀው የ2025 አፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ የዘንድሮ የክብር ተሸላሚዎች ታውቀዋል።
ኖቫ ኮኔክሽን ያወጣው መግለጫ እንደሚጠቁመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ አትሌት መሰረት ደፋር፣ ድምፃዊ መሃሙድ አህመድ፣ ባለሀብቱ ጆ ማሞ እና ሾው አቅራቢው ሰይፉ ፋንታሁን የዘንድሮ ተሸላሚዎች ሆነዋል።
አመታዊ የእውቅና ሽልማት ስነ ስርአቱ በአሜሪካና በአፍሪካ በሙያቸው ታላቅ ሥራ የሰሩ ግለሰቦችን ለማክበር የሚሰናዳ ሲሆን በየአመቱ ከስፖርት፣ ከስነ ጥበብና ከስራ ፈጠራ ዘርፎች ለማህበረሰቦቻቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦና ለለውጥ ላደረጉት የላቀ ተሳትፎ ከየዘርፉ ተመርጠው የሚሸለሙበት መድረክ ነው።
አፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ እስካሁን ለአራት ጊዜያት ተካሂዷል።
ከዚህ ቀደም እውቅና ከተሰጣቸው ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን( ቴዲ አፍሮ)፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ ድምፃዊ ኤኮንና አቶ በረከት ወልዱ ይገኙበታል።
ዘንድሮም በተለያዩ ዘርፎች አምስት ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያንን ለማክበርና እውቅና ለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል ያለው ኖቫ ኮኔክሽን በስፖርቱ ዘርፍ የኦሎምፒክ እና የአለም ሻምፕዮን ሜዳሊያዎች ባለቤት አትሌት መሰረት ደፋር፣ በቢዝነስ ዘርፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ባለሃብቱ ጆ ማሞ፣ በስነ ጥበብ ዘርፍ አንጋፋው ድምፃዊ መሃሙድ አህመድ፣ እና ታዋቂው የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያ ሰይፉ ፋንታሁን ተሸላሚዎች ይሆናሉ ብሏል።
"ዝግጅቱ በጊፍት ሪል ስቴት የአቅራቢ ስፖንሰርነት የሚታገዝ ሲሆን በእለቱ የዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ሴናተሮች፣ ከንቲባዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረጋላቸው በርካታ እንግዶች ይገኛሉ። ተሸላሚዎቹ ከግዛቶቹና ከተማዎቹ ተወካዮች የእውቅና ሰርተፍኬት ይበረከትላቸዋል" በማለት መግለጫው አስታውቋል።
የሽልማት ዝግጅቱ በሜሪላንድ ስቴት ሲልቨር ስፕሪንግ በሚገኘው ሲቪክ ህንፃ ኦክቶበር 12 ምሽት በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች በሚገኙበት ይከናወናል።
-መሠረት ሚድያ-



