ከ2,500 በላይ የአቢሲኒያ ባንክ ሰራተኞች ከስራቸው ሊቀነሱ መሆኑን ተናገሩ፣ ባንኩ በጉዳዩ ዙርያ ለሚድያችን ምላሽ ሰጥቷል
(መሠረት ሚድያ)- አቢሲንያ ባንክ ከ2,500 በላይ ሠራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑን እና ለዚህም ሲባል በርካታ ሰዎችን ወደ ግዜያዊ የሰራተኛ ቋት ውስጥ እያስገባ መሆኑን የሚገልፁ ጥቆማዎች ለሚድያችን ደርሰዋል።
የባንኩ አመራሮች ካለፈው ወር ጀምሮ ስብሰባ ላይ እንደነበሩ የታወቀ ሲሆን አሁን ላይ ለሁሉም ቅርንጫፎች እያንዳንዳቸው ቢያንስ ሶስት ሠራተኛ እንዲቀንሱ እንደታዘዙ እነዚህ የባንኩ ሰራተኞች መረጃ ያሳያል።
"ሁሉን ነገራችንን መስዋዕት አድርገን በብዙ ደንበኞች ዘንድ ተወዳጅ ያደረግነው ባንካችን፣ በቢልዮን ብሮች እንዲያተርፍ ያደረግነው ባንካችን፣ ምንም ሳናስብ ድንገት ያለምንም በቂ ምክንያት ሰው ሊቀንስ እንደሆነ በግልጽ ተነግሮናል" ያሉ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሰራተኛ ናቸው።
"አሁን በደመ-ነፍስ ሥራ እየገባን ነው። እንዲሁ ሜዳ ላይ ልጆቻችንን፣ ትዳራችንን እና ተስፋችንን እንዴት እንዲሁ ይውደቅ?" ያሉት ሰራተኛው በተጠናቀቀው የባንኩ የአምስት ዓመት የስትራቴጂ ዘመን አፈጻጸም በፊት ከነበሩት ዓመታት ከነበረው የባንኩ የፋይናንሻል እና ፋይናንሻል ያልሆኑ አቋሞች አንጻር በብዙ እጥፍ ከፍ ያለ ሆኖ ይገኛል ይላሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳያዩት ስትራቴጂው በሚነደፍበት በ2019 (እ.ኤ.አ.) የባንኩ የሀብት መጠን ብር 56.9 ቢሊየን የነበረ ሲሆን የስትራቴጂ ዘመኑ በ2024 (እ.ኤ.አ.) ሲጠናቀቅ ብር 222.14 ቢሊየን ደርሷል፡፡
በተጨማሪም በተቀማጭ ገንዘብ መጠን ረገድ በ2019 (እ.ኤ.አ.) ብር 32 ቢሊየን የነበረ ሲሆን የስትራቴጂ ዘመኑ በ2024 (እ.ኤ.አ.) ሲጠናቀቅ ብር192 ቢሊየን ደርሷል፡፡ በትርፍ መጠንም አንጻር በ2019 (እ.ኤ.አ.) ብር 1 ቢሊየን አካባቢ የነበረ ሲሆን የስትራቴጂ ዘመኑ ሲጠናቀቅ ወደ ብር 5.83 ቢሊየን ከፍ ብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የባንኩ ቅርንጫፎች ከ337 ወደ 919 አድገዋል፣ እንዲሁም የደንበኞች ቁጥር ከ1.3 ሚሊየን ወደ 13 ሚሊየን ደርሷል።
ሚድያችን የተመለከታቸው ሰነዶች እንደሚያሳዩት አሁን ላይ በርካታ ሰራተኞች ወደ ግዜያዊ ሰራተኛ ቋት ወይም በባንኩ አገላለፅ 'resource pool' እንዲገቡ እየተደረጉ ይገኛሉ።
"አሁን ግዜያዊ ናችሁ ነው የተባልነው። ስንት ዓመት በቋሚነት የሰራን ሰራተኞች ጊዚያዊ ሰራተኞች ናችሁ ስንባል በጣም ተጨንቀናል፣ ይሄን resource pool ሰራተኛን ለማሰናበት ቅድመ ሁኔታ አርገው እያስቀመጡ ይገኛሉ" የሚሉት ሌላኛው የባንኩ ሰራተኛ ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ የሚካሄደው ይህ አሰራር የቤት ኪራይ መክፈል ያቃተውን ታች ላይ ያለውን ሰራተኛን የመገምገሚያ መንገድ አጠያያቂ ነው ይላሉ።
"ከቅርብ አለቃው ጋር በሥራ እና በተለያየ ምክንያት የተነጋገረ ሰራተኛ በቀል በሚመስል መልኩ በሙሉ ወደ ግዜያዊ ሰራተኛ ቋት ዉስጥ ነው ያስገቡት። ብቻ በጣም ያሳዝናል፣ ምን እንደሚባል ግራ ያጋባል" በማለት ሁኔታውን ገልፀዋል።
"በዛሬው ዕለት እንኳን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተውን ስማችንን አጥፍታችኋል በማለት ዛቻ አድርገውብናል፣ ምንም አታመጡም የሚል መልስ ሰተውናል። ስለዚህ የአቢሲኒያ ባንክ ጉዳይ ሰፊ ሽፋን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፣ ወደሚመለከተው አካልም ብታደርሱልን እና መጠየቅ ያለበትን ሰው ብታናግሩልን" በማለት ሰራተኞቹ መልዕክት ለሚፍያችን ልከዋል።
አቢሲኒያ ባንክ ለመሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ በሰጠው አጭር ምላሽ ሰራተኞችን ለመቀነስ ወይም ለማባረር እቅድ የለውም ብሏል።
"እነዚህ ወደ 'resource pool' ዝርዝር ውስጥ የገቡ ሰራተኞች ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ የስራ ማስፋፊያ ስራ ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋሉ፣ ያላቸው ክህሎት እየታየ የሰው ሀይል ፍላጎት ባለበት ቦታ ይመደባሉ" ያለው ባንኩ ይህም ስራውን ለማስፋት ከማገዙ በተጨማሪ የተሳለጠ አሰራር እንዲኖር ያደርጋል ብሏል።
-መሠረት ሚድያ-






