መንግስት ያመቻቸውን ቤት ለማግኘት ተበድረው 25 ፐርሰንት ክፍያ የከፈሉ መምህራን የቤቱ ግንባታ ሳይጀመር ወለድ ለመክፈል መቸገራቸውን ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- ከስድስት ሺህ በላይ መምህራንን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው እና በ57 ማህበራት ለተደራጁ መምህራን የቤት ግንባታ ይጀመራል የተባለው የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ነበር።
በወቅቱ ተደጋግሞ እንደተነገረው መንግስት 24 ቢሊዮን ብር የሚገመት መሬት በነፃ ከማቅረቡ በላይ የዲዛይንና የፋይናንስ አማራጮችን በማመቻቸት ለመምህራን ያለውን ክብር በተግባር አሳይቷል።
ይህን ተከትሎም ጥር 27/ 2018 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስጀምረዋል ተብሎ ለሚድያዎች ተነግሮ ነበር።
እነዚህ ስድስት ሺህ መምህራን 25 በመቶ በመቆጠብ 3.8 ቢሊየን ብር የቆጠቡ ሲሆን ቀሪውን 75 በመቶ በመንግሥት በኩል የብድር ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውም ይፋ ተደርጎ ነበር።
ይሁንና መሠረት ሚድያ ከበርካታ መምህራን እንደሰማው 25 ፐርሰንት ከከፈሉ ግንባታው በአጭር ግዜ ተጠናቆ ቤት ትረከባላችሁ ቢባሉም የመሠረት ድንጋይ ከመጣል ባለፈ ግንባታ እየተካሄደ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
"እኛ ከ6 ሺህ በላይ መምህራን በጠቅላላው 5 ቢሊየን ብር ከየትም ከየትም ብለን ተበድረን ከፍለናል። በቅርብ ወራት ግንባታው አልቆ ቤታችን እንደምንገባ አብስረውን መሠረተ ድንጋይ ከንቲባዋ እና አጋሮቻቸው ጣሉ። ከዚያ ጀምሮ እንዲህ ሆነ እንዲያ ሆነ እያሉ አሁን አይደለም ህንጻው ሊጀመር ቀርቶ ለምን ቆመ ብንል ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" የሚሉት አንድ ክፍያውን የፈፀሙ መምህር ናቸው።
ሌላኛው የአዲስ አበባ መምህር ደግሞ "አብዛኛው መምህር ከሶስት ከአራት ቦታ ተበድሮ የከፈለ ነው፣ አሁን ባለው ኑሮ ላይ እየተሰራ ላልሆነ ቤት ከፍተኛ ወለድ መክፈል እጅጉን ከብዶናል። ባዶ ሆዳችንን እያስተማርን ነው" ብለዋል።
የቤቶቹ ግንባታ እንደተጀመረ በአንዳንድ የመንግስት ሚድያዎች ቢነገርም ጉዳዩ ትክክል እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
"25 ፐርሰንት ቁጠባ ማለት ምን ማለት ነው? በትንሹ የሁለት ሚሊዮን ብር በጣም ትንሿ ቤት 500 ሺህ ብር በአንድ ጊዜ ቁጠባ ከመምህሩ ይፈለጋል ማለት ነው፣ ከፍ ሲል ደግም ይቀጥላል። እንግዲህ ይህንንም ከፍለን ነው የምንሰቃየው" ያሉት ሌላኛው መምህር በየጊዜው የሚጠየቁ ተጨማሪ መዋጮዎች ለተለያዩ ስራዎች እየተባለ ኑሮውን የባሳ አክብዶታል ይላሉ።
ባለፉት ጥቂት አመታት "የማህበር ቤት ግንባታ" በሚል በየጊዜው የተደራጁና እስከ 5 ቢልዮን ብር ያሰባሰቡ የመምህራን ማህበራት እስከ አሁን አንዳቸውም ቤት አለመገንባታቸው ታውቋል።
-መሠረት ሚድያ-



