ለ25 ዓመታት የተገነባ ራዕይ: ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ብሄራዊ ፋይዳው
በዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ
የ25ኛ ዓመቱን ያከበረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ዕሁድ በደመቀ እና በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። የዚህ ተቋም የ25 ዓመት ጉዞው ብሄራዊ አንድምታ ጥልቅ እና ዘርፈ ብዙ ነው። ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ስፖርታዊ፣ ትምህርታዊ፣ ከጤና ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ፋይዳዎቹ የበረከቱ ናቸው። በተለይም ትምህርታዊ ፋይዳውን በዋናነትም ብሄራዊ አንድምታውን ይህ ጹሁፍ ተመልክቷል። ለዚሁም እንደመነሻ ባለፈው ሳምንት ሀሙስ የአሜሪካው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም ባንክ ኦፍ አሜሪካ (Bank of America) ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ታሪካዊ የአጋርነት ስምምነትን ማንሳት ይቻላል።
ስምምነቱ የስፖርታችንን ስብራት ወደ ብስራት መለወጥ እንደምንችል ያሳየ አጋጣሚ ነው። 25 አመታትን ቆጥሮ በመዘከር የመጣ ስኬት ብቻ ሳይሆን በራዕይ፣ በእቅድ፣ በዘመናዊ አካሄድና በተቀናጀ ስርአት የተገኘ የልፋት ውጤት ነው። ለአገራችን የስፖርት ዘርፍም ትልቅ መልዕክት የያዘ የአጋርነት ውል ጭምር ነው።
ለ25 ዓመታት የተገነባ ራዕይ
ለታላቁ ሩጫ ጅማሮ መሰረት መጠናከር ድርሻውን እንዳበረከት ሰው፣ ዝግጅቱ የታላቅነት ተስፋን ሰንቆ ተፀንሶ የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ውድድር እስከመሆን መብቃቱን ተመልክቻለሁ። ዋናው መሰረት የተጣለውም ገና ከጅማሬው ነበር። ግልፅ አላማና ግብ ይዞ፣ የአንድ ቀን መድረክ ብቻ ሳይሆን አመታትን አሻግሮ የሚመለከት ራዕይ ሰንቆ፣ ባህል ወግና ቅርስን ለአለም የማስተዋውቅ አጀንዳ አንግቦ እንዲሁም ሚሊዮኖች ሩጫን እንደ አንድ የህይወት ክፍላቸው እንዲቆጥሩት አስቦ የተቋቋመ፣ ይህንንም ያሳካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም ሆኗል።
ለዚህ ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደውና ቀዳሚው ሰው የታላቁ ሩጫ መሰረት ጣይ ታላቁ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ነው። ሀይሌ በአለም አደባባይ ኢትዮጵያን ከማስጠራቱ ባለፈ ሩጫ መለያችን መሆኑን በታላቁ ሩጫ ያሳየ ተምሳሌታችን ነው። ሌላው ደግሞ ሪቻርድ ኔርውርካር ሙያን ከባለሙያ ስራን ከስነምግባር አገናኝቶ ታላቁ ሩጫን ቅርፅ አስይዞ ተቋሙን በሁለት እግሩ እንዲቆም ካስቻሉት ጥቂቶች መካከል ሪቻርድ ኔርውርካር ቀዳሚው ነው። ሪቻርድ ለስራው የነበረው ትጉህነት እንዲሁም ለእቅድና ለግቡ የሚጠቀመው ስልት በወቅቱ አብረነው ለነበርነው በሙሉ የሚጋባና በአርአያነት የሚጠቀስ ነበር። ዳግማዊት አማረ ደግሞ ተቋሙን በበሰለ አደረጃጀት አንፃ በስኬታማ አመራር ጠብቃ ቅብብሎሹን ያሳደገች ተጠቃሽ መሪ ነች። እናም እነዚህ መሪዎችና ባልደረባዎቻቸው አንድ የውድድር መድረክ ብቻ አልፈጠሩም። ህብረትን ያስተዋወቀ በየአመቱ የሚናፈቅ ሁሉን አሰባሳቢ ሀገራዊ ብሄራዊ ተቋም አበረከቱልን እንጂ!
የትርጉም ጽንሰት እና ስፖንሰርሺፕ
አንድ ማህበረሰብ ለነገሮች የሚሰጠውን ትርጓሜና ትርጓሜውም ተቀባይነትን አግኝቶ የሚስተናገድበትን ፍቺ በተለያየ መንገድ ያገኛል። አንዳንዴ በልማድ ሌላ ጊዜ በተሞክሮ ሲልም የአንድን ነገር መረዳት በተረዳበት ፍቺ ልክ ቀድሞ ለማህበረሰቡ ያካፈለውን ሰው ትርጓሜ በስፋት በመቀበል፣ ወዘተርፈ ሊሆን ይችላል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ስፖንሰርሺፕ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ወይም አስተሳሰብ ነው። ስለ ስፖንሰርሺፕ በሀገራችን ያለው አስተሳሰብና ትርጓሜ እጅጉን የተዛባ፣ የተዛነፈና የተሳሳተ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ስፖንሰርሺፕ የሚወሰደው እንደ ስጦታ፣ ልግስና አልያም እርዳታ ነው።
እውነተኛ ስፖንሰርሺፕ ንዋየ መዋልን በማፍሰስ አዎንታዊ የጥቅም ምላሽ እንደሚገኝበት በመጠበቅ የሚፈፀም የሰጥቶ መቀበል የንግድ ልውውጥ ነው። ስምምነቱ በገንዘብ አልያም በአይነት ሊሆን ይችላል። የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በተለያየ መንገድና አካል ሊፈፀምም ይችላል። ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት። በተለያዩ መድረኮች ወይም ዝግጅቶች ለምሳሌ እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባሉት ላይ ወይም በግለሰብ ለምሳሌ ሀይሌ ከአዲዳስ ጋር አልያም ከተቋም ጋር ለምሳሌ ከሊግ፣ ከብሄራዊ ቡድን፣ ከአለም አቀፍ ዝግጅት አልያም ከስታዲየም ስያሜ ሊሆን ይችላል። የገበያ ምላሽን ደግሞ ይጠብቃል። ለምሳሌ አንድ ድርጅት ራሱ ተቋሙን ወይም ምርቱንና አገልግሎቱን ለህዝብ ማስተዋወቅ፣ ስለ ምርቱና አገልግሎቱ አስተማሪ መረጃዎችን ማቅረብ፣ ለገጽታ ግንባታ ጠቀሜታ ማዋል፣ በመጨረሻም የሽያጭና ሌሎች ግብረ መልሶችን ያካትታል።
ስፖንሰር አድራጊው ተቋም ገንዘቡን፣ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ስፖንሰር ለሚደረገው አካል የሚያቀርበው ለተመልካቹ፣ ለተሳታፊው፣ ለደንበኛው ወይም ለደጋፊው በመድረስ ትስስሩ የሚፈጥርለትን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የቢዝነስ አላማዎቹን ለማሳካት ነው። ለዚህ ደግሞ ስፖንሰርሺፕ አራት መሰረታዊ የንግድና የተግባቦት ደረጃዎችን ይከተላል። የመጀመሪያው ግንዛቤን መፍጠር ወይም እይታን መጨመር ነው። ህብረተሰቡ ስፖንሰር አድራጊውን እንዲያውቀው ማድረግ ቀዳሚ ስራ ይሆናል። የስፖንሰሩን ምርት፣ ምልክት ወይም አገልግሎት ማሳወቅ ይጠበቃል። ሁለተኛው ስለ ስፖንሰሩ ማስረዳት ወይም ማስተማር ነው። የመጀመሪያውን የስፖንሰርሺፕ ደረጃ አስታኮ አገልግሎቶችን እና ምርቶችን ከሌሎች ተመሳሳይ በገቢያው ውስጥ ካሉ ተወዳዳሪዎች የሚለዩባቸውን ባህርያትንና ተመራጭነትን ማስረዳትና አጉልቶ ማውጣት ማስቻል ነው። ሶስተኛው ደረጃ የስፖንሰሩን ገጽታ መገንባት ነው። ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና መልካም ምስልን በሰዎች አእምሮ ውስጥ ማስረጽ ነው። አራተኛውና የመጨረሻው ሽያጭ ነው። የደንበኛን ፍላጎት ያማከለ፣ በታማኝነት ሽያጭ ማከናወን ነው። የማንኛውም ስፖንሰር ዋነኛ ግብ ደግሞ ሽያጭ ነው። የሶስቱ ደረጃዎች የሂደት መጨረሻም አራተኛው ላይ ማለትም ሽያጩ ላይ ማረፍ ይሆናል።
ብዙ ጊዜ ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎች ዝርዝር የስፖንሰርሺፕ ባህሪና ትግበራ ለመማርና ለማጥናት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ አልያም መፅሀፍትን የሚያገላብጡ ብዙ ናቸው። በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርት ተቋማት ግን እንደ እኔ እይታ ይህንን ማድረግ ይበረታታሉ፣ ነገር ግን የግድ ላይላቸውም ይችላል። ምክኒያቱም አገር በቀል ተሞክሮውንም ማኑዋሉንም ከፊታቸው ያገኙታል። ለዚህም ታላቁ ሩጫ ለባለፉት 25 አመታት በዘርፉ የፈፀመውን ስኬት ማጥናት ሁነኛ አማራጭ ነው።
የባንክ ኦፍ አሜሪካ አጋርነት ብሄራዊ አንድምታ
በስፖንሰርሺፕ ውስጥ “Reverse Image Effect" የሚባል መርህ አለ። አንድ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ታላቅ ብራንድ በአንድ አገር ከሚገኝ ስፖርታዊ ተቋም ጋር በስፖንሰርሺፕ አጋርነት ለመስራት ሲስማማ፣ የአለም አቀፍ ተቋሙ ታላቅነት፣ ተቀባይነት፣ ክብር፣ ተአማኒነት፣ ወዘተርፈ ያሉ አዎንታዊ ገጽታዎች ወደ ስፖርታዊ ተቋሙ ትርጉም ባለው መልኩ የመሻገር አቅማቸው የተሳለጠና ያየለ መሆኑን በርካታ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶች አረጋግጠዋል። ባንክ ኦፍ አሜሪካ መምጣቱም ታላቁ ሩጫ የነበረውን ተቀባይነት፣ ክብር፣ ተአማኒነት፣ታዋቂነት ወዘተርፈ በአገርና አለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ያሳድጋል። ለሌላ የንግድና የስፖንሰርሺፕ አቅምም ተጨማሪ ጉልበት ይፈጥራል፣ በር ይከፍታል።
የሁለቱ ተቋማት የአጋርነት ስምምነት ለታላቁ ሩጫ ከሚኖረው “Reverse Image Effect” ባሻገርም ለመላው የኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። በባለሙያ የሚመራ፣ ለገበያ የሚያበቃ አወቃቀር ለፈጠረ አገራዊ ተቋም አለም አቀፍ ድርጅቶች አብረው ለመስራት እንደሚመጡ ማሳያ ጭምር ነው። በሀገራችን ያሉ የእግርኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቮሊቦልና ሁሉም ስፖርቶች በምን መንገድ ራሳቸውን ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚያሳይ የማንቂያ ደውል ጭምር ነው።
እግር ኳስና የሚያስፈልገው አስቸኳይ ለውጥ
ከሁለት አመት በፊት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጋር በመቀናጀት ሁለት አመት የፈጀና በሀገራችን እግርኳስ ልማት ዙሪያ ያጠነጠነ ጥልቅ እና ሰፊ ጥናት ተካሂዶ በመጸሃፍ መልክ ለሊጉ አዘጋጅቼ አቅርቢያለሁ። ጥናታዊ ፅሁፉ 370 ገፅ ያሉት ከ140 ሀገራት በላይ ተሞክሮን ያካተተ ከ15 የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለድርሻ አካላት ማለትም ከፌዴሬሽኑ፣ ከክለቦች፣ ከተጫዋቾች፣ ከወኪሎች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከምሁራንና ከሌሎች የተውጣጡ ከ90 በላይ ሰዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግ የተዘጋጀ ነበር። በተጨማሪም ሀገር አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ አለም አቀፋዊና የፊፋ ፖሊሲ ተሞክሮዎች የተመለከተ፤ የህግ ማእቀፎችን ያጣቀሰ፣ ከ200 በላይ የምርምር ጥናት ፅሁፎችን ያማከረ ጥልቅ፣ ሰፊና ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና አገር በቀል የልማት ፍኖተ ካርታ ያቀረበ የምርመራ ውጤት ነው። እንደ አንድ ዜጋም ያለኝን የሰጠሁበት እስካሁንም በትምህርት ሞያዬ ካካፈልኳቸው የሳይንሳዊ ጥናታዊ ጽሁፎች ልዩ እና ቀዳሚ ቦታ የምሰጠው የስራ ውጤት ነው።
የጥናቱ ውጤት ደግሞ ግልፅና አጭር ነበር። በኢትዮጵያ እግርኳስ አሁን ያለው አሰራር በተለይ በፋይናንስ በኩል ፍሬ አልባ ብክነት መሆኑን ያሳያል። በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከመንግስት በጀት ድጋፍ ነው። አብዛኞቹ በአማካይ በአመት 75 ሚሊየን ብር አካባቢ ያወጣሉ። ከዚህ ውስጥ 75% ያህሉ የሚውለው ለደሞዝ ክፍያ ነው። ቀሪው ለትራንስፖርትና ለሌሎች አቅርቦቶች ይከፈላል። ለመሰረተ ልማት፣ ለማርኬቲንግና ለረጅም ጊዜ ልማታዊ እቅድ የሚውለው ግን ኢምንት ነው። ይህ ደግሞ ዘለቄታዊነት ያለው የስፖርት እድገት ግንባታ አይደለም። አሸዋ ላይ ውሃ ሲያፈሱ እንደመኖር እንጂ።
ክለቦችን በማህበረሰብ ባለቤትነት የማስተዳደር ሃገራዊ መፍትሄ
በጥናቱ ነጥረው ለወጡት ውስብስብ እና ሥር ሰደድ ችግሮች መሰረታዊ መፍትሄው ማህበረሰቡን የክለቦች ባለቤት አድርጎ በሀገር ሰው ሀገራዊ እድገት የማምጣት ሞዴልን መከተል ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ የሚፈቅደውም የሚያዘውም ይሄንኑ ነው። ፖሊሲው በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ እንዳስቀመጠው ማህበረሰቡ የክለብ ባለቤት ይሆናል፤ መንግስት የስፖርት ልማትን ያመቻቻል፤ ያግዛል፤ ይላል። ከዚህ በተቃራኒ እና ፖሊሲውን በተጻረረ መልኩ በተግባር የሚታየው የክለቦች ባለቤትነት ግን በአብዛኛው (ከጊዮርጊስ እና ቡና በስተቀር) የተያዘው በአካባቢያዊ የመንግስት መዋቅሮች ነው። እዚህ ጋር 'በመንግስት መዋቅሮች ባለቤትነት መያዝ' እና 'በአካባቢያዊ የመንግስት አካላት ባለቤትነት መያዝ' ለየቅል መሆናቸውን ልብ ሊሉ ይገባል።
ጥናቱ የክለቦች ባላቤትነትን ከአካባቢያዊ የመንግስት አካላት ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ስር ማውጣት የእግርኳሱ ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ችግሮች የመጀመሪያው መፍትሄ መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል። በጥናቱ ምክረ ሀሳብ መሰረትም (በተጓዳኝም ህጋዊውን የፖሊሲ አቅጣጫ ለመከተል) የአንድ ክለብ የባላቤትነት ድርሻ መጠን ድልድልን እንደሚከተለው አስቀምጧል (በዚህ ዙሪያ የበለጠ እና ጥልቅ ትንታኔ ለማግኘት መጸሃፉን ይመልከቱ)፦ የተመዘገበ ደጋፊ 30%፣ ህዝብ 40%፣ እንዲሁም መንግስት 30% ድርሻ መያዝ ነው። ህዝብ የሚለው ቃል ደግሞ ሰፊ እና አቃፊ ነው። ይሀም በአካባቢው የሚኖሩ ግን በደጋፊነት ያልተመዘገቡ ነዋሪዎች፣ ክለቡ በሚገኝበት ያሉ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች፣ የሆቴልና ሞቴል ባለቤቶች፣ ባንኮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቢራ ፋብሪካዎች፣ ዲያስፖራዎችና ሌሎችን ያካትታል። በረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን መጨመር ይቻላል።
ይህ ሞዴል የክለብ አመራሮች ላይ ተጠያቂነትን ይፈጥራል እና ብቁ የስፖርት ንግድ አስተዳዳሪዎች ክለቦቹን እንዲመሩ ይጋብዛል። በተለይ ከፖለቲካ አመራሮች ጣልቃ ገብነት በራቀ መልኩ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ፣ በሞያ ብቃት እና አቅም ላይ የተመረኮዘ የስፖርት አመራርን ከነተጠያቂነቱ ለመመደብ ያስችላል፤ የስፖርት ንግድ ባህልን ለማስረጽ የተመቸ ይሆናል፣ ፈጠራ የታከለበት የገቢ ምንጭ ለመተግበር የሚያበረታታ አውድን ይፈጥራል። ከሁሉ በላይም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስፖርታዊ እና ባህላዊ እውነታዎች ጋር የታረቀ እና ዘለቄታነት ያለው የእግር ኳስ ልማት ማስፈን ያስችላል። በጥቅሉም አገር በቀል የክለቦች ባለቤትነት ሞዴሉ ክለቦች በራሳቸው ፈጠራ እንደ ታላቁ ሩጫ ገቢ አመንጭተው ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ፣ የአካባቢያዊ መንግስት አካላትም አሸዋ ላይ ከሚያፈሱት ውሃ ይለቅ በጀቱን ለደሃው ህዝባችን ትምህርት ቤት፣ ጤና ኬላ፣ የኮብል-ስቶን መንገድና የቤት ግንባታ ላይ እንዲያውሉት ያስችላል፤ በዋናነትም ለረጅም ጊዜ ርቆን የቆየውን የእግር ኳስ ብሄራዊ ድል ለማግኘት ጭላጭል የሚሰጠን፣ በጊዜ ሂደትም የሚያጎናጽፈን ዘላቂነት ያላው አካሄድ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
ተምሳሌቱ ደግሞ አጠገባችን ይገኛል
በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርት ተቋማት ስኬታማ የስፖርት ተቋም እንዴት እንደሚገነባ ለማወቅ ከሀገር ውጪ ማየት አይጠበቅባቸውም። ትልቁ ተምሳሌት እዚሁ ሀገር ቤት ይገኛል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተግባር ተፈትኖ በባለሙያና በጠንካራ አመራር ተመርቶ በማህበረሰቡ ታቅፎ ራሱን በማስታዋወቅና በመሸጥ ስኬታማ መሆኑንን በተግባር አሳይቷል። ብዙ ክለቦችና ፌዴሬሽኖች ያቃታቸውንና እስካሁን የሚታገሉበትን ራስን ችሎ መውጣትን ራስን መሸጥን አሳክቷል። ከትንሽ ሃሳብ ተነስቶ ብሄራዊ ተቋም ሆኖ የአለም አቀፍ አጋሮችን ቀልብ ስቧል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ሌሎቹ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ተቋማት ተመሳሳይ የማርኬቲንግ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ቢገኝም ሰንሰለቱን በጥሶ ወጥቷል። ልዩነት ማምጣትን ፈልጎ ብቻ ሳይቀመጥ ተለይቶ ወጥቷል። ስፖርትን እንደ ቢዝነስ ወስዶ ማህበረሰቡን አሳታፊና አጋር እንጂ የሩቅ ተመልካች ሳያደርግ ተንቀሳቅሶ ግቡን አሳክቷል።
ታላቁ ሩጫ ቤት ውስጥ ስለ ስፖንሰርሺፕ ጥልቅ መረዳትና ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ መልፋት ጭምር አለ። ከተለምዷዊው የስፖንሰር ግንዛቤ ወጣ ብሎ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ራስን ማስተዋወቅ፤ ምርትና አገልግሎትን ማስረዳት፣ ገጽታን መገንባት፣ ብሎም ምርትና አገልግሎትን የመሸጥ አስተሳሰብ የሰረፀበት ተቋም ነው። ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር የተደረገው የስፖንሰርሺፕ ስምምነትም ድንገት የመጣ ሲሳይ አይደለም። ከሁለት አስርት አመታት ከግማሽ በታታሪነት በፕሮፌሽናል አመራርና የገጽታ ግንባታ ጥረት የመጣ የልፋት ውጤት ነው።
በመንግስት ትከሻና በጀት ላይ ላሉ ክለቦች፣ ሊጎችና ፌዴሬሽኖች ታላቁ ሩጫ ቀላል ግን ጠንካራ መልዕክት አስተላልፏል። ተቋም እንዴት እንደሚመራ ከአጋሮች ጋር እንዴት ስምምነት እንደሚፈፀም በተግባር አሳይቷል። ለዚህም ነው ወደ ውጪ ተመልክቶ ጥናት ፍለጋ ከመባዘን አጠገባችን ያለውን ታላቁ ሩጫ በተምሳሌትነት መውሰድ የሚያስፈለገው። አርአያ ፍለጋ የውጭ ሀገር ተሞክሮን ከመፈለግ ይልቅ በየአመቱ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሺዎች አንድ ቤተሰብ ሆነው የሚውሉበትን መድረክና ተቋም እንድንመለከት የግድ የሚለን።
አርአያነትና የብር እዮቤል በአል አከባበር
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 25ኛ አመቱን ከማክበሩ ጎን ለጎን ሀገራዊ አርአያነቱን አሳይቷል። አንድ የስፖርት ተቋም በስነ ምግባር በንግድ ሃሳብና እቅድ ተመርቶ ስኬታማ ሲሆን ሌላው አለም ሌላው ተመልካች ማስታወሻ ይይዛል። አብሮ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ይዞ ይመጣል። ለዚህ ደግሞ የባንክ ኦፍ አሜሪካ አጋርነት አንዱ ማሳያ ነው። ይህ ከስፖንሰርሺፕ ስምምነት በላይ ነው። ለ25 አመታት በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ የተገነባ ፍኖተ ካርታና የስራ ድምር ውጤት ነው።
ይህ ምን ያሳያል? እ.ኤ.አ. በ2006 በታላቁ ሩጫ አማካይነት በእንግሊዝ አገር የስፖርት ማኔጅመንት ስማር አንድ መጣጥፍ ለጋዜጣ ፅፌ ነበር፤ ርዕሱ "በታላቁ ሩጫ ሁሉም አሸናፊ ነው" ይላል። ለኔ ታላቁ ሩጫ የጎዳና ላይ ውድድር ብቻ አይደለም።
ከስፖርትነቱ ባለፈ የጤናማ አኗኗር ማሳያ የማህበራዊ ህይወት ምሳሌ የታሪክና የባህል ማስተዋወቂያ ማዕከል ጭምር ሆኗል። በተጨማሪ ህዝብን ወደ አንድ ያመጣ ትውልድን ያነሳሳ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን ጠብታ የጨመረ በአለም የኢትዮጵያን ምስል በበጎ ያሳወቀ እንዲሁም ሩጫ ባህላችን መሆኑን ያሳየ ብሄራዊ ተቋም ለመሆን የበቃ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የበለጠ ድጋፍና ጥበቃ ክብርና ምስጋና ለተቋሙና ለመሪዎቹ ያስፈልጋል። በስፖርቱ ዘርፍ ሀገርን የመገንባት ስራ ላይ ናቸውና ይበልጥ እገዛ ያስፈልጋቸዋል።
የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት
የማጠቃለያ ሃሳቤ ምስጋናና የደስታ መልዕክት ይሆናል። በቅድሚያ ለባለራዕዩ ታላቁ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ያለኝን አክብሮትና አድናቆት መግለፅ እፈልጋለሁ። በአለም አደባባይ በእግሮቹ ተአምር ሰርቶ ሰንደቃችንን ከፍ አድርጎ ብሄራዊ መዝሙራችንን አዘምሮ ሀገራችንን አስጠርቷል። ካስለመደን ድልና ሜዳሊያ በኋላም ሀገር ማስጠራቱን ቀጥሎበታል። እንደግለሰብ እኔንም በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት የምርምር እና የማስተማር ዘርፍ እንድሰማራ መነሻ ሆኗል። በአገሪቷ ሩጫ የህይወታችን አንዱ ክፍል እንዲሆን አንድነትን የሚፈጥር መሰባሰቢያ መድረክ ፈጥሮልናል። ሀይሌ ታላቁ ሩጫን ወልዶልናል። ታላቅ ምስጋና ይገባዋል።
በታላቁ ሩጫ ጅማሬ ቢሮ ውስጥ ከነበሩ ሁለት/ ሶስት ባለሙያዎች አንዱ በመሆኔ እድለኛ ነኝ። መሰረትን መጣል ከባዱ ስራ ነው። ለ25 አመት በወጥነት በጠንካራ መሰረት በራዕይ በአላማና ግብ ማስቀጠል ብሎም ስኬታማ ማድረግና ለዛሬ ማብቃት ደግሞ ዋነኛው እና ትልቅ ስኬት ነው። ይህ ሁሉ በእድል አልመጣም። በከፍተኛ ደረጃ አመራርና ያለመሰልቸት በመስራት የመጣ ውጤት ነው። ለዚህም ሌላኛው ተመስጋኝ ሪቻርድ ኔርውርካር ይሆናል። የእሱ የላቀ የስራ ባህል፣ በሳል አመራርና እቅድ ታላቁ ሩጫን ወደ ላቀ ደረጃ አሻግሮታል። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ትልቁ ዝግጅት ሆኗል። ታላቅ ምስጋና ይገባዋል።
ዳግማዊት አማረ ሌላኛዋ ምስጋናና አድናቆት የሚገባት የታላቁ ሩጫ የጀርባ አጥንት ነች። ተቋሙን በላቀ አመራር በማስቀጠልና በማሳደግ እዚህ ደረጃ አድርሳዋለች። ታላቅ ምስጋና ይገባታል።
በመጨረሻ ታላቁ ሩጫን አምናችሁበት ይህንን የአጋርነት ስምምነት ለፈፀማችሁት ባንክ ኦፍ አሜሪካ እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁ። ታላቁ ሩጫ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ሌሎች የስፖርት ተቋማት ደግሞ ከዚህ ተማሩ ማለት እፈልጋለሁ። አገር በቀል ተሞክሮውም ማኑዋሉም ከፊታችሁ ነው።
ስለ ፀሀፊው
ዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ናቸው። ለታላቁ ሩጫ ጅማሮ መሰረት ከጣሉት አንዱ የሆኑት ዶ/ር ጋሻው ይህንን ተሞክሮ ወደ አሜሪካ በመውሰድ ግራንድ አፍሪካ ረንን መስርተዋል፤ ዘንድሮ ሰባተኛ አመት ውድድሩን በደማቁ በዋሽንግተን ዲሲ አከናውኗል። በስፖርት ስፖንሰርሺፕ፣ በስፖርት ቢዝነስና ማርኬቲንግ ዙሪያ በርካታ መፅሀፍትን የፃፉ አለም አቀፍ ተቋማትን የሚያማክሩና የሚያስተምሩ ምሁር ናቸው። በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል ደግሞ የዶክትሬት ተማሪዎችን በስፖርት ቢዝነስ ዙሪያ ያማክራሉ። ዶ/ር ጋሻው እስካሁን 10 መፅሀፍትን አሳትመዋል። በስፖርት ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ከ100 በላይ የሳይንሳዊ ምርምር የህትመት ውጤቶችን ለአንባቢው አቅርበዋል።





Thank you for all , Haile