ኪሳራ ላይ የሚታሰበው 2.5% ግብር ጉዳይ
በዋሲሁን ጂ. ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- የዛሬ አመት አካባቢ ያቋቋማኩት አንድ ድርጅት ነበረ። ነገሮች እንዳሰብኩት ስላልሄዱ ድርጅቱ ወጪ እንጂ አምስት ሳንቲም ገቢ አልነበረውም።
በዚህ የተነሳ 'እንደውም ድርጅቱን ልዝጋው ወይስ ትንሽ ልታገስ?' እያልኩ ግራ መጋባት ውስጥ ነበርኩ።
በዚህ መሀል ታዲያ አመታዊ ግብር ማሳወቂያም ጊዜ ደረሰና ለማንኛውም ላሳውቅ በሚል ዛሬ ለማሳወቅ ዶክመንቴን ሰብስቤ ገቢዎች ሄድኩኝ። ምንም ገቢ ስላልነበረኝ ከፋይ እሆናለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር።
ግብር አተማመኑ ግን እንዴት ቢሆን ጥሩ ነው?
ለማስረዳት ያህል ምንም ገቢ ባይኖረኝም ወጪዬ 1,000,000 ብር ነው እንበል። መጀመርያ በንግዱ ዘርፍ መሰረት 21% ግብር ታሰበ። ይህም 210,000 ብር ይሆናል። ልብ በሉ እንገዲ ገቢዬ ዜሮ ብር ነው፣ ወጪዬ ላይ ነው የሚሰራው።
ከዛ ይህ 210,000 ብር ዋናው 1,000,000 ብር ወጪዬ ላይ ተደምሮ አጠቃላይ 1,210,000 ብር ይሆናል። ከዛም የሱን 2.5% ማለትም 30,250 ክፈል ተባልኩ።
'እንዴት ሰው ኪሳራ ላይ ሆኖ ክፈል ይባላል?' ብዬ ብጠይቅም ከላይ የመጣ ነው ምንም ማድረግ አንችልም ነው መልሳቸው። እና ነገሩ ግራ ነው ያጋባኝ።
ብዙ አወዛጋቢ ወሳኔዎችን ሰምቼ አውቃለሁ፣ ግን ይሄኛው ተለየብኝ:
1) ግብር ማለት እራሱ ምን ማለት ነው ? አንድ ግለሰብ አንዳች ያገኘው ጥቅም ሳይኖር እንዴት ነው ወጪ ላይ ተቆሞ ግብር የሚሰራው?
2) እንደው ትርፍ እንኳ ቢገኝ ለእንደኔ አይነቱ እራሱን ለመቀየር ለሚፍጨረጨር ለንግዱም ጀማሪ ለሆነ ወጣት እንደውም የእፎይታ ጊዜ በመስጠት እንዲጠነክር ይደረጋል እንጂ ጭራሽ በኪሳራ ላይ ሌላ ወጪ በመጨመር እንዳያንሰራራ መደረግ አለበት?
3) እነሱ ወጪዬን ማወቅ የቻሉት ካፒታሌን በአግባቡ አስመዝግቤ ወጪዬንም ከዛው አካውንቴ ደረሰኝ እየተቀበልኩ በመፈፀሜ ነው። ይሄስ ሰው ካፒታሉን በአግባቡ እንዳያስመዘግብ፣ ወጪውንም ከአካውንቱ ይልቅ በስውር እንዲያደርግ የሚያስገድድ አይሆንም?
4) ስሰማ መንግስት ይሄን ማድረግ የጀመረው ብዙዎች ግብር ላለመክፈል ለአመታት በኪሳራ ስለሚያሳውቁ ነው አሉ። እንደኔ አይነቱ ጀማሪ ታዲያ አብሮ መጎዳት አለበት? ለአመታት እንደዚያ የሚያደርጉትን መከታተል እና ገና ጀማሪ ለሆነው ደግሞ የምርም ከስረን ከሆነ በትክክል የመዳኘት እድል ሊሰጠን አይገባም?
5) አንድ ነጋዴ ማትረፍ አይደለም ምንም ገቢ ሳይኖረው በወጪው ብቻ ግብር የሚከፍል ከሆነ ሰውስ እንዴት ነው ደፍሮ ወደ ንግድ ሊገባ የሚችለው? ምክንያቱም ከከሰረ መክሰሩ ሳያንስ ሌላ የወጪ ግብር የሚባል ነገር ይጠብቀዋል።
ብቻ እኔም በቅርብ ያናገርኳቸው ሰዎችም ሊገባን አልቻለም። እስኪ ያልተረዳነው ነገርም ካለ አስተያየት ስጡን።
አመሰግናለሁ
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
*መሠረትሚድያ*



