የቴሌቭዥን ግብር ከመብራት ሀይል ጋር አያይዘው እየከፈሉ ያሉ ዜጎች የኢትዮጵያ ቴሌዥን በጎን ሌላ ተመሳሳይ ግብር እየጠየቃቸው መሆኑን ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- "ማንኛውም የቴሌቪዥን ባለቤትለሚጠቀምብት ለእያንዳንዱ ቴሌቪዥን በዓመት ብር አንድ መቶ ሃያ ብር የቴሌቪዥን ባለቤትነት እና አገልግሎትፍቃድ ክፍያ መክፈል ይኖርበታል።"
ይህ ከላይ የተቀመጠው የቴሌቭዥን ግብርን በተመለከተ የወጣው አዋጅ ነው።
ይሁንና በበርካታ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ችግር ገጥሟቸዋል: ይህም ከመብራት ጋር አያይዘው ከሚከፍሉት በተጨማሪ ሌላ ክፍያ አምጡ መባላቸው ነው።
"እኔ በምኖርበት ቦሌ አራብሳ አካባቢ የቴሌቪዥን ግብር ክፈሉ በሚል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠን ነው። የቴሌቪዥን ግብር ከመብራት ጋር እየከፈልን እንደሆነ ብናስረዳቸውም ታዘን ነው በሚል ማዳመጥ አይፈልጉም። ለማን አቤት እንደምንል ግራ ገብቶን እንገኛለን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ማስጠንቀቂያ እያደሉ ያሉት። ብዙ ነዋሪም ቴሌቭዥናችን ይወሰድብናል በሚል ውዥንብር ተደናግጦ ከፍሏል" የሚሉት ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ ነዋሪ ናቸው።
የቴሌቭዥን ዓመታዊ ክፍያ ካልከፈላቹ በማለት አንዳንድ አጭበርባሪዎችም ህዝቡን እያስጨነቁት እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
"በኮዬ ፈጬ የሚገኙ አጭበርባሪዎች 500 ብር እየተቀበሉን ይገኛሉ። በአዋጁ ደግሞ ለመኖሪያ ቤት የሆነ ቴሌቪዥን በመብራት ሀይል በኩል እንደሚከፈል ያሳውቃል" የሚሉት ሌላ የከተማው ነዋሪ ናቸው።
አዋጁ በአንቀፅ 18 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የቴሌቪዥኑ አገልግሎት ለመኖሪያ ቤት በሆነ ጊዜ በዚህ አንቀፅ ንዑስ-አንቀጽ 1 ያለው ክፍያ አፈፃጸም በየወሩ በማስላትወይም በዓመት አንድ ጊዜ በኢትዮጵያየኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል እንዲሰበሰብ ይደረጋል ይላል።
"እኛ መብራት በምንሞላ ጊዜ አብረን እየከፈልን ነበር ማለት ነው። ግን በድጋሚ ይህንን ክፈሉ እያሉ እያስገደዱ እና እያስጨነቁን ይገኛሉ" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
በርካታ ጥቆማ ሰጪዎች ጉዳዩን ለማስረዳት ወደሚመለከተው የመንግስት ቢሮ ሲሄዱ 'ከበላይ ታዘን ስለሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፣ ክፈሉ' እያሏቸው መሆኑን ይናገራሉ።
"በኮዬ ፈጬ የቴሌቪዥን ግብር ካልከፈላችሁ ቲቪ እንወርሳለን እያሉን ነው፣ ይህ በግልፅ የሚነገረን ነገር ነው። እንዴት በአንድ ቲቪ ሁለቴ ግብር ይጠየቃል?" በማለት ሌላ የኮዬ ፈጬ አካባቢ ይጠይቃሉ።
በዚህ ዙርያ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ማብራርያ ለመጠየቅ ያረግነው ሙከራ አልተሳካም።
-መሠረት ሚድያ-





