በመምህራን የማህበር መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ላይ በካሬ እስከ 82 ሺህ ብር የሚደርስ ያልተጠበቀ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ
(መሠረት ሚድያ)- በመንግስት መሬት አቅራቢነት በተጀመረው የመምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ላይ በቅርቡ ይፋ እጅግ ከፍተኛ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑን ለሚድያችን እየደረሱ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በሆነው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (AASTU) ስር በሚገኘው የመምህራን ማህበር የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ላይ በቅርቡ ይፋ የተደረገው እጅግ ከፍተኛ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በአባላቱ መካከል ከፍተኛ ቅሬታንና ውጥረትን መፍጠሩ ተሰማ።
የፕሮጀክቱ ተሳታፊ የሆኑ መምህራን ለመሠረት ሚድያ እንደገለጹት ቀደም ሲል ከተስማሙበት የዋጋ ተመን ውጭ በአሁኑ ወቅት ከ134% እስከ 238% የሚደርስ ያልተጠበቀ ጭማሪ ተጭኖባቸዋል።
ይህ ጉዳይ የመምህራኑን አቅም ያላገናዘበና የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ሰበብ በማድረግ የተፈጠረ ህገ-ወጥ አሰራር ነው በሚል በፅኑ እየተኮነነ ይገኛል።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ውስጥ ከመምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት እና ከዩኒቨርሲቲው ተወካዮች ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ቢሆንም ምንም ዓይነት አዎንታዊ የለውጥ ውጤት ሳይገኝ መበተኑን የኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።
በስብሰባው ላይ የቀረበው አዲስ የዋጋ ዝርዝር (Bill of Quantities) እንደሚያሳየው ሙሉ በሙሉ ያለቀለት (Full Finish) የአንድ ብሎክ ባለ 10 ፎቅ (G+10) ህንፃ ግንባታ በትንሹ 923,457,635 ብር የተመደበለት ሲሆን እንደ ኮንዶሚኒየም ፊኒሺንግ ያላለቀው ደግሞ ያለታክስ በትንሹ 498,868,530 ብር ሆኖ ቀርቧል።
ይህ አዲስ ተመን መምህራን በህዳር ወር ላይ ከከፈሉት የ25 በመቶ ቅድመ ክፍያ አንጻር ሲሰላ በ3 እጥፍ ገደማ ጭማሪ ያሳየ ነው።
የማህበሩ ኮሚቴ ተወካይ በስብሰባው ዙሪያ ሲናገሩ "በፊት 25% ክፈሉ ተብለን ተበድረን ስንከፍል ህዳር ላይ የነበረው ዋጋ አሁን በ3 እጥፍ ጨምሯል። 'ካልከፈላችሁ ግንባታው አይሰራም' የሚል አስገዳጅ አቅጣጫ ነው የተሰጠን። ነገር ግን እንደ ኮሚቴ ባደረግነው ውይይት መሠረት አንድም የማህበሩ አባል ያላመነበትን እና ያልተስማማበትን ሰነድ ላይ በጭራሽ እንደማንፈርም ተስማምተናል" ብለዋል።
ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ጭማሪው በሌሎች ተቋማትም ይፋ እየተደረገ ነው።
ከጉዳዩን በተመለከተ ሌላኛው መረጃ አቅራቢ መምህር እንደገለጹት ግንባታው ገና ከመሬት ሳይነሳ እና ኮንትራክተሮቹ አፈር ከመቆፈር ውጭ ምንም ዓይነት መዋቅራዊ ስራ ሳይሰሩ "ብር ካልተጨመረልን አንሰራም" በሚል ስራ ማቆማቸውን ገልጸዋል።
መምህሩ አክለውም"የመምህሩ ደሞዝ ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ እየታወቀ የተወሰኑ የመንግስት አካላት ከኮንትራክተሮቹ ጋር በመመሳጠር እኛን ወደ ከባድ ችግር ውስጥ ከትተውናል። የ25 በመቶ ቅድመ ክፍያውን ራሱ ከተለያዩ ቦታዎች ተበድረን ነው የከፈልነው፣ አሁን ግን ዋጋው በብዙ እጥፍ ጨምሯል እየተባለ ግራ ተጋብተናል" ሲሉ ተናግረዋል።
በከፍተኛ ቁጭት ውስጥ የሚገኙ ሌላኛው መምህር የዋጋውን ዝርዝር በማነፃፀር እንዲህ ብለዋል: "ከ8 ወራት በፊት የአንድ ካሬ ሜትር የኮንስትራክሽን ዋጋ 35,000 ብር ነው ተብለን ነበር የቆጠብነው። አሁን ግን ያለምንም በቂ ምክንያት ዋጋውን ወደ 82,000 ብር በላይ አሳድገውታል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው መንግስት መሬቱን በነፃ እንደሰጠ የተነገረን ሲሆን ይህ አሁን የተጠየቅነው 82,000 ብር ለአንድ ካሬ ሜትር ግንባታ ብቻ የተሰላ መሆኑ ነው" ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
የማህበሩ አመራሮች በሰጡት ምላሽ የተገነነውን የዋጋ ዝርዝር (BOQ) ለአባላቱ እንደሚልኩና አባላቱ በጥልቀት ተመልክተው የተደጋገሙ ወይም የተጋነኑ ክፍታቶች ካሉ መሠረታዊ የህንፃውን ጥራት ሳይነኩ ማስተካከያ (Recommendation) ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ከዚያ ባለፈ ግን ዋጋውን የመቀነስ አቅም እንደሌላቸውና ለቀጣይ ከበላይ አመራሮች ጋር የሚነጋገሩበት ጊዜ እንደሚመቻች አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ መምህራኑ የወቅቱን የዋጋ ግሽበት ያላገናዘበና አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በመሆኑ መንግስት እና የሚመለከታቸው ከፍተኛ አካላት አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት እንዲያደርጉና መፍትሄ እንዲሰጧቸው በፅኑ እየጠየቁ ይገኛሉ።
| መሠረት ሚድያ |




