ቢቢሲ ላይ በመቅረብ ቃለ መጠይቅ ያረገችውን ዶ/ር ማህሌት ጉዕሽን ጨምሮ በአንድ መዝገብ ተከሰው የነበሩ ዘጠኝ የጤና ባለሙያዎች በዛሬው እለት ተፈቱ
(መሠረት ሚድያ)- ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ እያካሄዱት ካለው የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ግንቦት 6, 2017 ዓ/ም የቢቢሲ 'Focus on Africa' ፕሮግራም ላይ በመቅረብ ጥያቄዎቻቸውን ያብራራችው ዶ/ር ማህሌት ጉዕሽን ጨምሮ በርካታ የጤና ባለሙያዎች መታሰራቸው ይታወሳል።
የጤና ባለሙያዎቹ በመላው ኢትዮጵያ እያካሄዱት ካለው የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ በፀጥታ አካላት ከተያዙ በኋላ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር።
መሠረት ሚድያ የተመለከተው እና ፌደራል ፖሊስ በፅሁፍ ያቀረበው የግዜ ቀጠሮ መጠየቅያ ወረቀት ዘጠኝ ተከሳሾች 'ሁከት እና ብጥብጥብ' ባማነሳሳት ወንጀል እንደተጠረጠሩ ይገልፃል።
ይሁንና በዶ/ር ማህሌት መዝገብ ላይ ያሉትን ስምንት ሰዎች ጨምሮ በርካታ የጤና ባለሙያች በዛሬው እለት ከእስር መለቀቃቸውን መሠረት ሚድያ አረጋግጧል።
በአንድ መዝገብ ተከሰው የነበሩት ዶ/ር ማህሌትን ጨምሮ ዶ/ር ሳሙኤል ሀይሉ፣ ዶ/ር ሚኪያስ አለም፣ ዶ/ር ሩት አማረ፣ ዶ/ር ኃይለየሱስ ንጋቱ፣ ሚካኤል ተሰማ፣ ጃፋር አብዱጂላል፣ ኡስማን አዋይ እና አለባቸው ፈቄ ነበሩ። ሁሉም በዛሬው እለት መለቀቃቸው ታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሶስተኛ ፖሊስ ጣብያ ተይዘው ከነበሩ 30 ገደማ የጤና ባለሙያዎች መሀል አብዛኞቹ የተለቀቁ ሲሆን አሁንም ከነሱ መሀል ግን ያልተለቀቁ እንዳሉ ታውቋል።
ዶ/ር ማህሌት ከቤቷ ከተወሰደች በኋላ ለእስር መዳረጓ እና ከሌሎች በርካታ የጤና ባለሙያዎች ጋር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርባ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። ባለሙያዎቹ ያቀረቧቸው 12 ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ወደ ሙሉ የስራ ማቆም አድማ ጀምሮ መጀመራቸው ይታወሳል።
ፖሊስ በክሱ ላይ "ተጠርጣሪዎቹ ከጥር 2017 ዓ/ም ጀምሮ ሌሎች ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን፣ ከፀረ ሰላም ሀይሎች ጋር በመመሳጠር በመደራጀት እንዲሁም እንዲሁም ተልዕኮ በመቀበል በከተማ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አመፅ እንዲሁም ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ ለማድረግ" የሚል ውንጀላ ቁርቦባቸው ነበር።
ክሱ አክሎም "በሚሰሩበት ስራ ዘርፍ ታካሚዎችን አናክምም፣ አገልግሎት ፈላጊዎችን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት የስራ ማቆም አድማን ሲቀሰቅሱ" እንደነበር ይጠቅሳል።
ላለፉት ሁለት አመታት ስራ ላይ ያልነበረችው እና በቢቢሲ 'Focus on Africa' ፕሮግራም ላይ በመቅረብ የጤና ባለሙያዎቹን ድምፅ ያሰማቸው ዶ/ር ማህሌት ጉዕሽ የታካሚዎች ህይወት ማለፍን በተመለከተ የቀረበው ክስን ስራ ላይ እንዳልነበረች በመጥቀስ ስትከላከል ፖሊስ 'በውጭ ሃገራት ሆነው ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመተባበር' የሚል ውንጀላ ቀርቦባት ነበር።
መረጃን ከመሠረት!


