በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ድንገት በተከፈተ ተኩስ ሁለት ታዳጊዎች መገደላቸው ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ጎብዬ በሚባል አካባቢ ሁለት ታዳጊዎች ድንገት በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ገለፁ።
ሁለቱ ታዳጊዎች የተገደሉት በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ድንገት በተከፈተ ተኩስ ነው ተብሏል።
ከሟቾቹ አንዱ ደሳለ ከቤ የተባለው ታዳጊ የተገደለው ከቤቱ በር ላይ መሆኑን የገለፁት ምንጮች ከሟቾቹ በተጨማሪ በአንዲት የልጆች እናት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በዚሁ አካባቢ በተመሳሳይ መንገድ ወጣቶች መገደላቸውን የገለፁት ኗሪዎቹ የመከላከያ ሰራዊት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ተኩስ በተከፈተ ቁጥር የገፈቱ ቀማሾች ሕፃናት፣ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች ናቸው ሲሉ አክለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ከሶስት ቀን በፊት የፋኖ ሀይሎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ወገራ ወረዳ ገደብጌ ከተማ ውስጥ የመንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በምላሹ ወታደሮች የከተማው ነዋሪ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ከሆስፒታል ምንጮች እና ከገደብጌ ከተማ ነዋሪዎች የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ 11 ሰዎች በዚህ ጥቃት ተገድለዋል።
"ከፋኖ ጋር ምንም ንክኪ የሌላቸው የ80 ዓመት ሽማግሌን ጨምሮ አምስት ሰዎች አንድ ቦታ ላይ ተገድለዋል፣ ከቤታቸው እየተጎተቱ ወጥተው ተረሽነዋል" በማለት አንድ የከተማው ነዋሪ ተናግረው ተጨማሪ ነዋሪዎች በሌሎች የከተማው አካባቢዎች እንደተገደሉ ጠቁመዋል።
መረጃን ከመሠረት!



