(መሠረት ሚድያ)- የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ የ2026 ተሸላሚዎችን ዛሬ በይፋ አስታወቀ። በዘንድሮው ሽልማት በየሙያ ዘርፋቸው ላስመዘገቡት ከፍተኛ ስኬት፣ ለአመራር አስተዋጽኦቸውና ለማኅበረሰብ ላበረከቱት አገልግሎት አምስት ታዋቂ ግለሰቦች ተመርጠዋል። ተሸላሚዎቹ በአሜሪካ፣ በአፍሪካዊ ዲያስፖራ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥራቸው በጎና ዘላቂ ተፅዕኖ ያሳደሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የ2026 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች:
• ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን (“ሉሲ” ወይም “ድንቅነሽ”ን በማግኘታቸው በዓለም የሚታወቁ ታዋቂ የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ)፣
• አትሌት ፖል ቴርጋት (ታላቁ የረጅም ርቀት ሯጭና የኦሎምፒክ ሜዳሊያ አሸናፊ)
• ኢዮብ “ጆ” ማሞ (ውጤታማ ሥራ ፈጣሪና የንግድ መሪ)
• አለምፀሐይ ወዳጆ (ስመጥር የኪነ ጥበብና ባህል ሰው እንዲሁም የሰብዓዊነት አገልግሎት አበርካች) እና
• ማክዳ አሰፋ (በግል የቴሌቭዥን ሚዲያ ታሪክ ቀዳሚ የሆነዉን ebs ቴሌቪዥን መስራች የነበሩት የአ/ቶ አማን ፍሥሐጽዮን ባለቤትና ከጎናቸው የቆዩ የሚዲያ ቢዝነስ መሪ) ናቸው።
እነዚህ አምስት ተሸላሚዎች በሳይንስ፣ በስፖርት፣ በንግድ፣ በኪነ ጥበብና ባህል እንዲሁም በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች የተመዘገቡ የላቀ ስኬቶችንና አስተዋጽኦዎችን የሚወክሉ መሆናቸው ተነግሯል።
ተሸላሚዎቹ ኦክቶበር 11፣ 2026 በሜሪላንድ በሚካሄደው የ2026 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ሥነ ሥርዓት ላይ በይፋ ይሸለማሉ።
“የ2026 ተሸላሚዎች ከተለያዩ የሙያና የሥራ ዘርፎች የመጡ ቢሆኑም እያንዳንዳቸው በስኬታቸው፣ በአመራራቸውና በአገልግሎታቸው ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኦክቶበር 11 ስኬታቸውን ለመዘከርና ያሳደሩትን በጎ ተፅዕኖ ለማክበር በታላቅ ጉጉት እንጠባበቃለን” ሲሉ የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ዳይሬክተር ዶ/ር ጋሻው አብዛ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ በስምንት ዓመታት ውስጥ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ባለፉት ስድስት የሽልማት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ለላቀ ስኬታቸውና አስተዋጽኦቸው 26 ግለሰቦች ተሸላሚ ሆነዋል።
ከዚህ ቀደም በስፖርት ዘርፍ የተሸለሙት መካከል ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ጉዳፍ ፀጋይ እና ትዕግስት አሰፋ ይገኙበታል።
በኪነ ጥበብና ባህል ዘርፍ አስቴር አወቀ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ሙላቱ አስታጥቄ እና ሰይፉ ፋንታሁን ተሸላሚዎች ሲሆኑ በንግድና ማኅበረሰብ አመራር ዘርፍ አቶ ግርማ ዋቄ፣ አቶ መስፍን ጣሰው እና አቶ በረከት ወልዱ ከሌሎች ተሸላሚዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ በሙያቸው፣ በአመራራቸውና በማኅበረሰብ አገልግሎታቸው በአሜሪካ፣ በአፍሪካዊ ዲያስፖራ እና ከዚያም ባሻገር በማኅበረሰቦች ላይ አዎንታዊና ዘላቂ ተፅዕኖ የፈጠሩ ግለሰቦችን የሚያከብርና የሚያስተዋውቅ መድረክ ነው። ለተጨማሪ መረጃ፦ www.africanrun.com
| መሠረት ሚድያ |



አፍሪካ ብሎ ኢትዮጵያውያንን መሸለም ምን የሚሉት ነው?