(መሠረት ሚድያ)- ዝነኛው የኬንያ የረጅም ርቀት ሯጭ ፖል ቴርጋት ኦክቶበር 10 ቀን 2026 በአሌክሳንድሪያ፣ ቨርጂኒያ በሚካሄደው ግራንድ አፍሪካን ረን የክብር እንግዳ ሆኖ እንደሚሳተፍ አዘጋጆቹ አስታወቁ።
ፖል ቴርጋት በዕለቱ ከዝነኞቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ስለሺ ስህን ጋር በክብር እንግድነት ይገኛል ተብሏል።
ፖል ቴርጋት በዓለም የረጅም ርቀት ሩጫ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ካላቸው አትሌቶች አንዱ ነው። አምስት ጊዜ የዓለም ክሮስ ካንትሪ ሻምፒዮን ሲሆን በኦሎምፒክ 10,000 ሜትር ሁለት ጊዜ የብር ሜዳሊያ አሸንፏል።
በ10,000 ሜትር፣ በግማሽ ማራቶን እና በማራቶንም የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ነበር። በ2003 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በመግባት፣ የማራቶንን ርቀት ከ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በታች ያጠናቀቀ የመጀመሪያው አትሌት ሆኗል።
ለኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ አድናቂዎች ደግሞ ፖል ቴርጋት ከአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር ባደረጋቸው እጅግ አጓጊ ፉክክሮች የማይረሳ ስም ነው። በተለይ በ2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ የ10,000 ሜትር ፍጻሜ ኃይሌ ገብረሥላሴ ቴርጋትን በ0.09 ሰከንድ ብቻ ቀድሞ ያሸነፈበት ውድድር እስከዛሬ ድረስ በኦሎምፒክ የረጅም ርቀት ሩጫ ታሪክ ውስጥ ከማይረሱ ፉክክሮች አንዱ ነው።
ከውድድር ስኬቱ ባሻገር ፖል ቴርጋት ለስፖርት እድገት፣ ለወጣቶች እና ለማህበረሰብ በሚያደርገው አስተዋጽኦም ይታወቃል።
የግራንድ አፍሪካን ረን ዳይሬክተር ዶ/ር ጋሻው አበዛ የፖል ቴርጋትን ተሳትፎ አስመልክተው “ፖል ቴርጋት ግራንድ አፍሪካን ረን የሚወክለውን መንፈስ፣ የላቀ ስኬትን፣ ትህትናን እና ለማህበረሰብ የመስጠት ቁርጠኝነትን የሚያንጸባርቅ አትሌት ነው። እሱን ከደራርቱ ቱሉ፣ ከጥሩነሽ ዲባባ እና ከስለሺ ስህን ጋር በአንድ ጠዋት ማግኘት ለማህበረሰባችንና በዕለቱ ለሚሳተፉ ሁሉ ትልቅ ክብር ነው” ብለዋል።
ግራንድ አፍሪካን ረን በ2026 ለስምንተኛ ዓመት ይካሄዳል። ዝግጅቱ የአፍሪካ አትሌቶች በአትሌቲክስ፣ በረጅም ርቀት ሩጫ እና በክሮስ ካንትሪ ያስመዘገቡትን አኩሪ ስኬት ለማክበር የተጀመረ ሲሆን ከማንኛውም ማህበረሰብ ለሚመጡ ሁሉ ክፍት ነው።
ባለፉት ሰባት ዓመታት አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ትዕግሥት አሰፋ እና ጉዳፍ ፀጋይን ጨምሮ በርካታ ዝነኛ አትሌቶች በግራንድ አፍሪካን ረን ተገኝተዋል። የዘንድሮው ግራንድ አፍሪካን ረን ቅዳሜ ኦክቶበር 10 ቀን 2026 በአሌክሳንድሪያ፣ ቨርጂኒያ ይካሄዳል። ተጨማሪ መረጃ በዚህ ድረ-ገፅ እንደሚገኝ ተጠቁሟል: www.africanrun.com
| መሠረት ሚድያ |


