ከሰሞኑ የጉምሩክ ኮሚሽን ላወጣው የስራ ቅጥር የኮታ ቁጥር ውስጥ ለመግባት እስከ 200 ሺህ ብር ጉቦ እየተጠየቀ መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን በቅርቡ ያወጣው የስራ ቅጥር አወዛጋቢነቱ ቀጥሏል።
ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ ከ2 ሺህ በላይ ስራ ፈላጊዎችን ለመቅጠር ለሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ኮታ ቢሰጥም እዚህ ኮታ ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ መጠን ያለው ጉቦ እየተጠየቀ መሆኑ ታውቋል።
መሠረት ሚድያ ያሰባሰባቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህን በአካማይ ከታክስ በፊት በወር 27 ሺህ ብር ደሞዝ የሚያስገኝ ስራ ለማግኘት ሀላፊነቱ የተሰጣቸው የመንግስት ሀላፊዎች በትንሹ 50 ሺህ ብር፣ ከፍ ሲል እስከ 200 ሺህ ብር እየጠየቁ መሆኑ ታውቋል።
ይህን ክፍያ መክፈል የቻሉ ኮታ ውስጥ እንደገቡ፣ ያልቻሉ ደግሞ ከቅጥሩ ውጪ እንደሆኑ ታውቋል።
"በጣም ተቸግሬ ተምሬ እና በአካውንቲንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ነበር፣ አሁን ግን ተስፋ ቆርጬ ቁጭ ብያለሁ። የማላመለክትበት የለም፣ ግን ሁሉም በዘመድ ነው" በማለት አንድ በዚህ መልኩ ክፍያ ተጠይቀው መክፈል ያልቻሉ እና ከኮታ ውጭ የሆኑ ምንጭ ለሚድያችን ጠቁመዋል።
"ለየከተማው የተሰጠው ኮታ ውስጥ ስምህ እንዲገባ ከ 50 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር በግልፅ እየተጠየቀ ነው፣ እኛ ገንዘብ የሌለን ምን እንሁን?" በማለት ገልፀዋል።
"እኛ ዘመድም፣ ገንዘብም የሌለን እውቀት ብቻ ያለን የደሀ ልጆች ምን እንሁን? በጣም ያማል፣ መከራ አይቼ ተመዝግቤ የፖሊስ እና ሌሎች መረጃዎች አሟልቼ ይህንን ሳይና ስሰማ በጣም ከፋኝ" ብለው የተሰማቸውን ተናግረዋል።
ለምሳሌ በባህር ዳር ከተማ ኮታው 54 ሲሆን ተጠባባቂ 16፣ በአጠቃላይ ድምር 70 ሰው መስፈርቱን በትክክል አሟልቶ ተመዝግቧል ተብሏል። በአጠቃላይ የተመዘገበው ሰው ደግሞ ከ500 እንደሚበልጥ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያሳያል።
"ጉምሩክ ኮሚሽን ኮታ ላኩ ያለው ባስቸኳይ ነው፣ እስከ ማክሰኞ ሰኔ 25 ማለት ነው። በዚህች ቀን ዘመድ ያለው እና ገንዘብ ያለው ገብቷል" ብለው ስሜ ሳይጠቀስ ማረጋገጫ መስጠት እችላለሁ ያሉት አንድ የከተማው የጉምሩክ ቢሮ ባልደረባ ናቸው።
ሌላኛ ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ "ቃሊቲ ጉምሩክ ድረስ ሄጄ ህገወጥ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ለማስረዳት ሞከርኩ። ሰሚ ግን አላገኘሁም፣ እኛ እነሱ መልምለው ያመጡትን መመዝገብ ነው ስራችን አሉኝ። ዋናው መስሪያ ቤትም ደውዬ ለመጠየቅ ሞከርኩ፣ እነሱም 'እኛ አይመለከተንም' የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል" ብለው ለሚድያችን ተናግረዋል።
ይህ የጉምሩክ የስራ ቅጥር ያስከተለው ውዝግብ በዚህ ብቻ አያበቃም።
በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮቹ የስራ እና ስልጠና ቢሮዎች በኩል የወጡትን 14 መመልመያ መስፈርቶች አሟልተው የተመለመሉ በርካታ ዜጎች ለፈተና እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ከሰሞኑ ከጉምሩክ ኮሚሽን ተደውሎላቸው እንዳልተካተቱ እንደተነገራቸው ጠቅሰዋል።
"በዋናነት የነገሩን በመደበኛ ፕሮራም የተመረቁ ብቻ ለፈተናና ቅጥር ታሳቢ እንደሚደረጉ ነው። ይህ ድርጊት ህጋዊም፣ ሞራላዊም ነው ብለን አናስብም" በማለት በአንድ ሀገር ውስጥ ባለ ህጋዊ የትምህርት ስርዐት ውስጥ ያለፉ ዜጎችን በዚህ መልኩ ማግለል ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።
መረጃን ከመሠረት!





