ከሁለት አመት በፊት ከኤድና ሞል ወረድ ብሎ በሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ ሽጉጥ በመተኮስ ሰው የገደለው ግለሰብ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ
(መሠረት ሚድያ- አባተ አበበ ይባላል፣ ልክ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ጓደኛውን ቦሌ ኤርፖርት ከሸኘ በኋላ ከምሽቱ 4 ሰአት ገደማ ከኤድና ሞል ወረድ ብሎ 'ፍለርት ላውንጅ' ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጥይት ተመትቶ ተገድሎ ነበር።
የሆነውን ሁሉ በአካባቢው የነበሩ የታክሲ ሹፌሮች እና የፍለርት ጠባቂዎች እንደተመለከቱ፣ ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ ግድያውን ከፈፀመ በኋላ ከአካባቢው መሰወሩን ተናግረው ነበር።
አባተን በመግደል የተከሰሰው ተስፋዬ ሆርዶፋ የተባለ ግለሰብ በዛሬው እለት በ20 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን የመንግስት ሚድያዎች ዘግበዋል።
ፋና እንደዘገበው የግራ ቀኝ ማስረጃን መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የግድያና የከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትህ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ህግ ተስፋዬ ሆርዶፋ በተባለ ግለሰብ ላይ በከባድ ግድያ ወንጀል ማለትም የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 ንዑስ ቁጥር 1ሀ እና የጦር መሳሪያ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ሁለት ክሶች ቀርበውበት እንደነበር ተመላክቷል።
"በወቅቱም ህገወጥ ሽጉጡን በመያዝ አምልጦ እንደነበር እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቅሶ ክስ ቀርቦበታል" ያለው ዘገባው ዐቃቤ ህግ ከክሱ ጋር የሰው ምስክር ዝርዝርና የተለያዩ ገላጭና አስረጂ የፎረንሲክ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።
ተከሳሹ የተለያዩ የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቶ የነበረ ቢሆንም የዐቃቢ ህግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል አለመቻሉ ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረበውን 3 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በደረጃ 2 በእርከን 36 መሰረት ሁለቱም ክሶች ተጠቃሎ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ታውቋል።
-መሠረት ሚድያ-



