"ኦሮማይ!… እንደገና! ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም ይምጣ!"-በአቶ ልደቱ አያሌው ለመሠረት ሚድያ የተላከ ( ክፍል 2)
3. ጦርነትን ለማስቀረት ትኩረት የሚያሻቸው ልዩ ጉዳዮች
3.1. ነገረ-ትግራይ
ሁልጊዜም ስለ ትግራይ ህዝብ ጉዳይ የሆነ ሀሳብ ለመስጠት ስሞክር “ድሮውንም አንተ የህወሀት ጠበቃ ነህ” የሚል ግልብና መቸም ቢሆን ማቆሚያ የሌለው ትችት ከአንዳንድ ወገኖች ሊቀርብብኝ እንደሚችል አስቀድሜ አውቃለሁ። ነገር ግን ከህዝብና ከሀገር ጥቅም አንፃር ፋይዳ አለው ብዬ እስካመንኩበት ድረስ በእኔ በኩል ዛሬም ሆነ ወደፊት ርዕሰ-ጉዳዩን ከማንሳት አልቆጠብም። ዛሬም በትግራይ ያለው ሁኔታ እየተላለቁ ከመፈራረሱ ስጋታችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ሀሳብ ልሰጥበት ወድጃለሁ። በኢትዮዽያ ፖለቲካ ነገሮችን ከግል ስሜትና አድልኦ /Bias/ ነፃ ሆነው በምክኒያት ለማየት የሚሞክሩ ፖለቲከኞች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው። ጉዳዩ ከትግራይ ጋር የተያያዘ ሲሆን ደግሞ የእነዚህ የጥቂቶቹ ሚዛናዊነትም ብዙውን ጊዜ ፈተና ላይ ሲዎድቅ እታዘባለሁ። ይህ የሚሆንበትን ምክኒያት የምረዳው ብሆንም እዚህ ላይ በግልፅ ባልናገረው እመርጣለሁ።
ትግራይንም ሆነ ህወሀትን በተመለከተ ያለን ከሚዛን የወደቀ አተያይ ግን በትናንቱ፣ በዛሬውም ሆነ በነገው የሀገራችን ፖለቲካ አንድ ዋና የችግር አንጓ እንደሆነ በእርግጠኛነት ስለምገነዘብ በእኔ በኩል ትኩረት ከምሰጣቸው አሳሳቢ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። ዛሬ ኢትዮዽያ ካሏት አስራ አንድ ክልሎች ውስጥ ለብልፅግና አገዛዝ ያልተንበረከከና ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚሞክር ብቸኛ ክልላዊ መንግስት ያለው በትግራይ ነው። አገዛዙ ቀደም ሲል የሁለት ዓመቱን ጦርነት ለማካሄድ የወሰነው፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም እስካሁን ድረስ በተለያዬ መንገድ እየሞከረ ያለው እንደ ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ ትግራይንም በሙሉ ቁጥጥሩ ስር ለማዋል ነው።
አገዛዙ ትግራይን በጫማው ስር ሳያንበረክክ እንቅልፍ ተኝቶ ለማደር የቻለ አይመስልም። የብልፅግና አገዛዝ ይህንን ፍላጐቱን ለማስፈፀም ሲል ህወሀትን በሽብርተኝነት ፈርጆ፡ ህጋዊ እውቅናውን ሰርዞ፣ በአመራሮቹ ላይ የእስር ማዘዥ አውጥቶ፣ የራሱን አሻንጉሊት አስተዳደር ጭምር አቋቁሞ በህግ ማስከበር ስም ሁለንተናዊ ጦርነት በትግራይ ላይ ያካሄደ ቢሆንም እስካሁን ፍላጐቱን ማሳካት ግን አልቻለም። አገዛዙ በዚያ የሁለት ዓመት ህዝብ ጨራሽ ጦርነት አንድ ሚሊየን በሚገመት ህዝብ ላይ ዘግናኝ ዕልቂት ከፈፀመ በኋላም ፕሪቶሪያ ላይ በተካሄደው ስምምነት ከህወሀት ጋር እንደገና ለመታረቅ፡ የሽብርተኛነት ፍረጃውን ለማንሳት፣ አሻንጉሊቱን መስተዳድር ለማፍረስና ህወሀትን በፓርቲነት እንደገና ለማዎቅ ተገደደ እንጅ እንደ ፍላጐቱ ህወሀትን ከምድረ-ገፅ አጥፍቶ ትግራይን በቁጥጥሩ ስር ለማዋል አልቻለም።
“አገዛዙ ትግራይን በጫማው ስር ሳያንበረክክ እንቅልፍ ተኝቶ ለማደር የቻለ አይመስልም”
ከዚህ ተጨባጭ ኪሳራ ቅንጣት ትምህርት መውሰድ ያልቻለው አገዛዝ እንደገና ሌላ መቋጫ የሌለው ጦርነት በአማራ ህዝብ ላይ ከፈተ። ይህም አልበቃው ብሎ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ግን ውጤቱ የበለጠ አስቀያሚ የሚሆን ስህተት ለመስራት እየተዘጋጀ ይገኛል። አሁንም እንደገና የህወሀትን እውቅና ለመሰረዝና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማክተሙን በአደባባይ በማዎጅ ወደ አዲስ የጦርነት ትርምስ ሊያስገባን እየተንደረደረ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ተሞክሮ ያልተሳካው የጦርነት አማራጭ ዛሬ የብልፅግና አገዛዝ ከብዙ አጋሮቹ ተነጥሎ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትና በፋኖ የተራዘመ ጦርነት ክንዱ የበለጠ ዝሎ፣ የኢኮኖሚ አቅሙ ተዳክሞ በሚገኝበት ሁኔታ የተለየና የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚል ዕምነት በበኩሌ የለኝም። የዛሬው ህወሀትን የማጥፋት እርምጃ ከትናንቱ የተለየ የሚያደርገው ድርጊቱ እየተፈፀመ ያለው በአገዛዙ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የትግራይ ልሂቃን ትብብር ጭምር መሆኑ ነው።
ከብልፅግና ሴራ በፀዳ አግባብ የትግራይ ህዝብ ዘላቂ ሰላም እንዲያገኝ ከመጣር ይልቅ የትግራይን ህዝብ ወክሎ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የፈረመውን ህወሀትን በዚህ መጠን ለማዳከምና ለማጥፋት መረባረብ በትግራይ የቆመውን ውጊያ እንደገና ከማስቀጠል ባለፈ ሌላ ፋይዳና ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ህወሀት በውስጡ በተፈጠሩ ቅራኔዎች ምን አልባትም በታሪኩ ገጥሞት በማያውቅ መጠን አሁን ላይ የበለጠ የተዳከመ መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም። ይሁንና ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በሀገሪቱ የመጣው የኃይል አሰላለፍ ለውጥ በህወሀት መከፋፈልና መዳከም ብቻ የሚገለፅ አይደለም። ህወሀት ካለፈው ጦርነት በብዙ ርቀት ብዙ ተዋጊ ኃይል በያዘበት፣ አንዳንድ የቀድሞ ጠላቶቹን ጭምር አጋር ማድረግ በቻለበት፣ ከሙሉ ከበባ ወጥቶ መግቢያ መውጫ ባገኘበት በአሁኑ ወቅት ህወሀትን እንደገና በጦርነት ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራ የትም መድረስ የሚችል አይመስለኝም።
የትግራይ ልሂቃን ከቀድሞው በተሻለ ዛሬ ላይ ህወሀትን መተቸት፣ መቃዎምና መታገል መጀመራቸው በወቅታዊነቱ ላይ ጥያቄ ቢኖረኝም ምክኒያታዊና የሚገባ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክኒያቱም የዛሬው ህወሀት በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚ የሀምሳ ዓመቱን የህወሀት ጥፋቶችና ድክመቶች ሁሉ ሰብስቦ ለመሸከም የተገደደ “ዕድለ-ቢስ” አመራር ጭምር በመሆኑ በብዙ መዋቅራዊ ችግሮችና ድክመቶች የታጨቀ ድርጅት ነው። ነገር ግን ይህንን በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተተበተበን፣ ዛሬም ቀላል የማይባል ማህበራዊ መሰረት ትግራይ ውስጥ ያለውን ድርጅት ታግሎ መለዎጥ የሚቻለው መቸ፣ እንዴትና እስከምን ድረስ ነው? የሚለውን ጥያቄ ከትግራይ ነባራዊ ሁኔታና ከአጠቃላዩ የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ጋር አስተሳስሮ በስክነት ማየት ተገቢ ይሆናል። በእኔ ዕይታ- ህወሀትን ታግሎ ለማጠናከር፣ ለመለወጥ ወይም ለማጥፋት ሲፈለግ የሚከተሉትን ቁም-ነገሮች ታሳቢ ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
አንደኛ- የፕሪቶሪያው ስምምነት ውጊያውን እንጂ ጦርነቱን በዘላቂነት ያላስቆመ መሆኑንና ህወሀትም ሆነ ትግራይ ገና በጦርነት ስነ-ልቦና ውስጥ ያሉ መሆናቸውን፣ ሁለተኛ- የህወሀት ህልውና መሰረዝ ወይም መጥፋት የፕሪቶሪያው ስምምነት ማክተምን በይፋ የሚያረጋግጥና ለጊዜው ቁሞ የነበረውን ውጊያ እንደገና የማስቀጠል ውጤት የሚኖረው መሆኑን፣ ሶስተኛ- በህወሀትና በአብዛኛው የትግራይ ህዝብ መካከል ያለው የሀምሳ ዓመታት ግንኙነት ከፖለቲካ በላይ የሆነ ስነ-ልቦናዊና ስሜታዊ /Sentimental/ ቁርኝት ያለው በመሆኑ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ሊለያይ እንደማይችል፣ አራተኛ- ሀገሪቱ ሰላሳ ሶስት ዓመት ሙሉ በስልጣን ላይ በቆየ፣ ሁሉንም ረግጦ የመግዛት ፍላጐት ባለው፣ የህወሀትን መጥፋት ቀዳሚ አጀንዳው ባደረገ አምባገነናዊና ጦረኛ አገዛዝ ስር ባለችበት በአሁኑ ወቅት ህወሀት በተለየ ሁኔታ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ ሊገኝ እንደማይችል፣ አምስተኛ- በትግራይ የተካሄደው ህዝብ ጨራሽ ጦርነት በዘላቂነት ባልተቋጨበት፣ ጦርነቱን ያካሄደው አገዛዝ አሁንም በስልጣን ላይ በሚገኝበት፣ የጦርነቱ እንደገና የመቀጠል ዕድል ሰፊ በሆነበት ሁኔታ የትግራይም ሆነ የህወሀት ቀዳሚ አጀንዳ ከማናችንም ፍላጐት በተለየ የማዕከላዊነትና የመዋጋት ብቃት መኖር እንጂ የዴሞክራሲያ እና የልማት መኖር ሊሆን እንደማይችል፣ ስድስተኛ- ህወሀት በአሁኑ ወቅት እየደረሰበት ያለውን ውስጣዊና ውጫዊ ጫናና ተፅዕኖ መቋቋም ተስኖት ቢፈርስና ቢጠፋ ትግራይን በብልፅግና ቁጥጥር ስር ከመውደቅም ሆነ ለሌላ የህልውና አደጋ ከመጋለጥ ሊታደግ የሚችል አዲስ የፖለቲካ ኃይል በቀላሉ ተጠናክሮ ሊዎጣ የማይችል መሆኑን፣ ሰባተኛ- ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ነባራዊ እውነታዎች ባልተለዎጡበት ሁኔታ አሁን ላይ ህወሀትን ማዳካምም ሆነ ማጥፋት የትግራይን ህዝብ ህልውና የበለጠ ለአደጋ የሚያጋልጥና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገዛዙን የስልጣን የበላይነት የበለጠ የማፅናት ውጤት የሚያስከትል መሆኑን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ- የትግራይ ህዝብ አስተማማኝ የህልውና ዋስትና ባላገኘበትና ሌላ ዙር ጦርነት በአካባቢው እያንዣበበ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ህወሀትን ከትግራይ ለመንቀል መሞከር ወንዝ እየተሻገሩ የጋለቡትን ፈረስ ለመቀየር እንደመሞከር የሚቆጠር አደገኛ መቀናጣት ነው። ከምንም ነገር በላይ ለትግራይ ህዝብ ዛሬ ላይ የሚያስፈልገው ውስጣዊ ልዩነትና ቅራኔን ሁሉ ለጊዜው ወደ ጐን አስቀምጦ የህልውናን ጉዳይ ቀዳሚና ዋና አጀንዳ አድርጐ ተባብሮ መቆም ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ- ህወሀት በከፍተኛ የህልውና ፈተና ውስጥም እያለ ለአካታችነትና ለህዝብ አንድነት መስራት፣ የትግራይን ህዝብ አማራጭ የፖለቲካ ሀይል የማግኘት መብት ከልብ ማክበር፣ በትግራይ የተፈጠረውን የወቅቱን መከፋፈል ለመፍታት የሚያስችል ሀቀኛ ዕርቅ ለማስፈን መጣር፣ እስካሁን ይዞት የመጣው የፖለቲካ መስመር ለትግራይም ሆነ ለኢትዮዽያ በብዙ እጅ ያልጠቀመ መሆኑን በመገንዘብ ራሱን በሀቅ መገምገምና ለአዲሱ ትውልድ የሚመጥን አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ መያዝ፣ “የጠላቴ ጠላት ወዳጀ” በሚል የተሳሳተ እሳቤ የኢትዮዽያ ታሪካዊ ጠላቶች ተባባሪ ከመሆን መቆጠብና የሰላምን አጀንዳ ከፕሮፓጋንዳ ጥቅም ባለፈ ልባዊ ስትራቴጂክ ዓላማና ግብ አድርጐ መስራት፣ ከሁሉም በላይ አሁን ላይ ሊፈነዳ የተቃረበውን ሌላ አውዳሚ ጦርነት ለማስቀረት አቅምና ሁኔታ በፈቀደለት መጠን ከልብ መታገል ይኖርበታል።
ከዚህ ውጭ በአንድ ደካማ ፓርቲ ላይ ያለ ጊዜውና ያለ ተገቢ መጠን የሚደረግ ጫና የባሰ ቀውስና ድክመት እንጅ አወንታዊ ለውጥና ሰላም ሊያመጣ አይችልም። በተለይም አዲስ የሽምቅ ተዋጊ ፈጥሮ የትግራይን ችግር ለመፍታት መሞከር የስህተቶች ሁሉ ስህተት ይሆናል።
ህወሀት ዋና መራሄ-መንግስት በነበረበት የሀያ ሰባት ዓመቱ ቆይታው ለዛሬው ውድቀት ምክኒያት የሆኑ አያሌ ጥፋቶች ሲፈፀሙና ሌላው ህዝብ ኢህአዴግን ሲታገል አብዛኛው የትግራይ ልሂቅ እያየ እንዳላየ አድፍጥ የተቀመጠ ወይም የኢህአዴግ ደጋፊ የነበረ ነው። ያ የትግራይ ልሂቅ ያኔ መራሄ-ህወሀት የሆነውን የኢህአዴግን ስህተቶች ለማረም ከሌላው ህዝብ ጋር በሞቆም ለመታገል ሞክሮ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ህወሀትም ሆነ የትግራይ ህዝብ ከገጠማቸው አደጋ መዳን በቻሉ ነበር። ኢትዮዽያም እንደ ሀገር ለዚህ ዓይነቱ ጨፍጫፊ የመራሄ-ኦህዴድ የብልፅግና አገዛዝ ባልተጋለጠች ነበር።
የትግራይ ልሂቅ ያን የወደፊት አደጋን አስቀድሞ ለማስቀረት የሚያስችል የለውጥ አጋጣሚ በከንቱ ካሳለፈ በኋላ ዛሬ ዙሪያው-ገደል በሆነበት ህወሀት ላይ ይህንን ያህል መረባረብ ከህወሀት በላይ ትግራይን ለበለጠ አደጋ የሚያጋልጥ ዳግም ጥፋት እንዳያመጣ መጠንቀቅ አለበት። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህወሀት ሲዳከም ትግራይ ለበለጠ አደጋ መጋለጧ፣ ትግርይም ስትዳከም ኢትዮዮዽያ ለበለጠ አደጋ መጋለጧ አይቀሬ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ህወሀት ዛሬ ላይ ለገጠመው ድክመትና ውድቀት ልሂቁ የራሱ የማይናቅ ድርሻ እንደነበረውም ሊረሳው አይገባም። በተለይም የትግራይ ህዝብ ጠንካራ አማራጭ ሀይል እንዳይኖረው በማድረግ ረገድ ልሂቁ የተጫዎተው ሚና ቀላል አይደለም። የትግራይ ልሂቅ ቢያንስ ዛሬ ላይ በርካታ የኦሮሞ ልሂቃን የመራሄ-ኦህዴዱን የብልፅግና አገዛዝ፣ በርካታ የአማራ ልሂቃን የአገዛዙን ዋና አጋር የሆነውን ብአዴንን በሚታገሉበት መጠን የትግራይ ልሂቃን የትናንቱን መራሄ-ህወሀት አገዛዝ ታግለውት ቢሆን ኖሮ የአሁኑ የትግራይም ሆነ የኢትዮዽያ ነባራዊ ሁኔታ በብዙ እጅ የተለየና የተሻለ በሆነ ነበር።
ነገር ግን ህሊና በእብሪት ተሞልቶ ነበርና፣ ወደፊት የኃይል ሚዛኑ በኢህአዴግ ውስጥም ሆነ በኢትዮዽያ ሲለወጥ የሚፈጠረው አደጋ ከባድ እንደሚሆን ለማስጠንቀቅ የሞከርን ሰዎች በወቅቱ እንደ ሟርተኛ ከመታየት ባለፈ ሰሚ አላገኘንም። በማዕከል የነበረውን ስልጣን ተነጥቆ ራሱ ዋና የጥቃት ሰለባ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ህወሀት በድንገት አቃፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መጠበቅም ግብዝነት ይመስለኛል። የቱንም ያህል ተቋማዊ ነፃነት እንዲኖር ብንፈልግ የኢትዮዽያ መንግስት፣ የብልፅግና ፓርቲና መከላከያ ሰራዊት አንድም-ሶስትም ሳይሆን አንድና-አንድ ሆኖ በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እየፈፀመ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ህወሀትና የትግራይ መከላከያ ኃይልም /TDF/ ሆነ ህወሀትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ ሶስት አካላት ሆነው ለማየት መሞከር ከምኞት ያለፈ ትርጉም የሚኖረው አይመስለኝም። የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ባልዋለበት ሁኔታም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የህግና የፖለቲካ አመክንዮ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። ከሁሉም በላይ ትክክለኛውን ጊዜና ሁናቴ ያልዋጀ ለውጥ ውጤቱ ጠቃሚ አይሆንም። ለምሳሌ የዚህ መጣጥፍ ፀሀፊ ሀገሬ ኢትዮዽያ የባህር-በር ባለቤት ብትሆን ከማንም ያላነሰ ደስተኛ በሆንኩ ነበር።
ከዚህ ፍላጐቴ በተፃራሪ የወቅቱን የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ የባህር-በር ጥያቄ የምቃዎመው ግን ጥያቄው የተነሳበት የጀርባ ዓላማ፣ ጊዜና ሁናቴ እንኳንስ የታሰበውን ጥቅም የሚያስገኝ ሀገሪቱን የበለጠ ዋጋ የሚያስከፍል ፈርጀ-ብዙ መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ ስለምገነዘብ ነው።
2010 ዓ.ም ላይ “ቲም ለማ” ወደ ስልጣን መጣ ሲባል ለውጡ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ኢህአዴግን “አታፍርሱት” ብየ እንደተከራከርኩት ሁሉ፣ ዛሬም እድሜ ልኬን የታገልሁትን ህወሀትን “አታፍርሱት” የምለው በተመሳሳይ መርህ ላይ በመቆም ነው እንጂ በተለየ ምክኒያት አይደለም። የኢትዮዽያዊነት ፖለቲካ አራማጅ እንደመሆኔ መጠን በአንድ ጉዳይ ላይ አቋም የምይዘው ከግሌ ወይም ከአንድ ቡድን ጊዜያዊ ስሜትና ፍላጐት በመነሳት ሳይሆን የሀገሪቱንና የህዝቧን የመካከለኛና የሩቅ ዘመን ዕጣ-ፈንታ ግምት ውስጥ አስገብቸ ነው። ስለሆነም፣ የትግራይ ልሂቃንም ሆናችሁ የህወሀትን መጥፋት የምትናፍቁ ሌሎች የሀገሪቱ ልሂቃን የወቅቱን የትግራይ ጉዳይ በስሜትና በጥላቻ ሳይሆን ልብ ገዝታችሁ በስክነት ብታጤኑት ተገቢ ይመስለኛል።
3.2. ተጠያቂነትና ሰላም
በአንድ የዕርስ-በርስ ጦርነት ውስጥ ባለ ሀገር ሰላም ለመፍጠር ለሚደረግ ጥረት እንቅፋት ከሚሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ የተጠያቂነት ጉዳይ እንደሆነ በርካታ በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያሳያሉ። በጦርነቱ ተሳታፊ ከሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ በወንጀል ተጠያቂና ተፈላጊ ሊሆኑ የሚችሉ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ካሉ እነዚህ ኃይሎች ተጠያቂነትን በመፍራት የሰላም እንቅፋት መሆናቸው አይቀሬ ነው። ይህ ችግር በእኛ ወቅታዊ ሁኔታ ተጨባጭ የሰላም እንቅፋት ሆኗል ማለት ይቻላል። በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝና አጫፋሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛዎቹ ተፋላሚ ኃይሎች ጭምር በውስጣቸው የተለያዩ ወንጀሎችን የፈፀሙ ቡድኖችንና ግለሰቦችን አቅፈው የያዙ ናቸው።
የእነዚህ ኃይሎች ወንጀለኛ መሆን ደግሞ በብዙ ዓለም-አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ሪፖርቶች ላይ ደጋግሞ የተመዘገበና ተመድንና አውሮፓ ህብረትን በመሳሰሉ ተቋማት ጭምር የሚታዎቅ ነው። ወደፊት በወንጀል እንጠየቃለን ብለው የሚሰጉ አካላት ስልጣናቸው “የነብር ጅራት” ስለሚሆንባቸው በቀላሉ አይለቁትም። በመንግስት ውስጥ ሲኖሩ የገቡበትን ጦርነት ሁሉ እያሸነፉ ዕድሜ ልክ በስልጣን ላይ ለመቆዬት፣ በተቃዋሚነት ደረጃ ያሉ ከሆነ ደግሞ የገቡበትን ጦርነት አሸንፈው ራሳቸው ወደ ስልጣን ለመውጣት እስከ መጨረሻው ይዋጋሉ እንጅ ጦርነቱ በሰላማዊ ድርድርና ዕርቅ እንዲፈታ አይፈልጉም። ይህ ችግር በኛ ሀገር አንድ ለሰላም መኖር እንቅፋት የሆነ መሰረታዊ ችግር ሆኗል። እኛ ግን ሁልጊዜም ትኩረት ሰጥተን የምንነጋገረው እንዴት ተጠያቂነት ይምጣ? በሚለው የተለመደ አጀንዳ ላይ ነው እንጅ የተጠያቂነትን ጉዳይ እንዴት አድርገን የሰላም እንቅፋት ከመሆን ልናስቀረው እንችላለን? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ አይደለም።
ተጠያቂነትን “ይቅር” ብሎ መከራከር ከሞራልና ከህግ፣ ከተጐጅዎች ስሜትና ችግሮች ወደፊትም እንደገና እንዳይደገሙ ከማድረግ አንፃር ተገቢነት የሌለው አቋም እንደሆነ እገነዘባለሁ። ነገር ግን በተጠያቂነት ምክኒያት ሰላምን በዘላቂነት የምናጣ ከሆነ፣ ሰላም በማጣታችንም የሌሎች ሚሊዬኖች ልጆቻችንን ህይዎት የምንሰዋ ከሆነ፣ ሄደን ሄደንም እንደ ሀገርና ህዝብ እየተላለቅን ወደ መፍረስ አደጋ የምንገባ ከሆነ ቢያንስ የተጠያቂነትን ጉዳይ እንዴት አድርገን ሰላምን በዘላቂነት በማያሳጣን አግባብ ልናስተናግደው እንደምንችል በድፍረት መነጋገር አለብን ብዬ አምናለሁ። በእኔ ዕይታ፣ ዋና የጦርነት መሀንዲስ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይንና የመከላከያ የጦር ጀነራሎችን ጨምሮ በርካታዎቹ የጦርነቱ ተሳታፊዎች በግልፅ እንዲነግሩን ባንጠብቅም በዚህ የተጠያቂነት ፍርሀት ውስጥ ያሉ ናቸው። ይህንን ስጋታቸውን በተዎሰነ ደረጃ የሚቀርፍ መፍትሄ ካላፈላለግን በስተቀር ጦርነቱን በሰላማዊ ድርድር በቀላሉ ማስቆምና እየተላለቁ ከመፈራረስ ራሳችንን መታደግ የምንችል አይመስለኝም። ስለዚህ የተጠያቂነትን ጉዳይ የሰላማችን እንቅፋት በማይሆን አግባብ እንዴት እንፍታው? በሚለው አጀንዳ ዙሪያ በድፍረትና በትኩረት መነጋገር አለብን ብዬ አምናለሁ። መልሱ ቀላል እንዳልሆነ ብገነዘብም በኔ በኩል ግን የተጠያቂነት ጉዳይ አጠቃላይ ህልውናችንን እንዲህ የሚፈታተን ውጤት የሚያስከትል ሆኖ ከተገኘ ተጠያቂነትን በከባድ የቅጣት መንገድ ሳይሆን አስተማሪ በሆነ የዕርቅና የይቅርታ ዕርምጃ የመፍታት ጉዳይን እንደ አንድ አማራጭ መፍትሄነት ማየት ተገቢ ነው እላለሁ።
የታጣቂዎቹ የህልውና ስጋት የሁላችነንም ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ሲገኝ ከተለመደው አካሄድ ወጣ ያለ መፍትሄ ማፈላለግ ተገቢ ይሆናል። ተጠያቂነትን ማስፈንን አስፈላጊ ቁም-ነገር ያደረገው ዞሮ-ዞሮ የሰው ልጆች ደህንነትና መብት መከበር ነውና- የተጠያቂነት ጉዳይ ራሱ ለሀገርና ለሰው ልጆች ደህንነት እንዲህ ትልቅ ጋሬጣ ሆኖ ከፊታችን ሲቆም ከፍትህም የሚቃረን የፖለቲካ የመፍትሄ አማራጭን መሻት የግድ አስፈላጊ ይሆናል እላለሁ። ስሜታችን እየኮሰኮሰንም ቢሆን በጉዳዩ ላይ ደፍረን እንነጋገርበት። ማጠቃለያ ሁላችንም እንደ ኃላፊነታችን መጠን በተናጠልና በጋራ የየድርሻችንን ከተዎጣን ጦርነትን በማስቀረትና ሰላምን በማስፈን ከፊታችን የተጋረጠውን እየተላለቁ የመፈራረስ አደጋ የመሻገር እድል ሊኖረን ይችላል። ይህንን ማድረግ ተስኖን እንደ እስካሁኑ አንዳችን ከሌላችን መፍትሄ እየጠበቅን፣ መስዋዕትነት በመክፈል ሳይሆን ለውጥን በባዶ ፍላጐትና ምኞት ለማግኘት እየተመኘን ከቀጠልን ግን ከፊታችን እየመጣ ያለው ተጨማሪ ጦርነት የመጨረሻችን መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህንን መገንዘብ ተስኖን የወቅቱን ጦረኛ አገዛዝ የምንደግፍ፣ ወይንም የአገዛዙ ተቃዋሚ ሆነንም እያለ ለሀገር የሚጠቅም እየመሰለን በተለየ ሁኔታ ለአንዳንዶቹ የአገዛዙ የተሳሳቱ አካሄዶች ተባባሪ የምንሆን ወገኖች ብዙዎች ነን። አገዛዙን በሁሉም ነገር መቃዎም ተገቢ ባይሆንም፣ በእኔ ዕይታ ግን-
በአሁኑ ወቅት በሀገር ብሄራዊ ጥቅም ሰበብ አሰብን ከኤርትራ ለመንጠቅ መሞከር እየተላለቁ የመፍረስ አደጋን የበለጠ አይቀሬ ማድረግ ነው።
በአሁኑ ወቅት አገዛዙ ህወሀትን ለማጥፋት የሚወስደውን እርምጃ መደገፍ እየተላለቁ መፍረስን መደገፍና መተባበር ነው።
በአሁኑ ወቅት አገዛዙ ፋኖንና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን በጦነት ለማጥፋት የያዘውን አቋም መደገፍ እየተላለቁ መፍረስን መደገፍና መተባበር ነው።
በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ድርድርና እርቅን ተቃውሞ መቆም እየተላለቁ መፍረስን መደገፍና መተባበር ነው።
በአሁኑ ወቅት ከሻዕቢያ ጋር ተባብሮ የኢትዮዽያን ችግር ለመፍታት መሞከር እየተላለቁ መፍረስን መደገፍና መተባበር ነው።
በአሁኑ ወቅት ጦርነትን ቋሚ የአስተዳደር ዘይቤው አድርጐ በህዝብ ላይ ጦርነት እያካሄደ ያለውን የብልፅግና አገዛዝ መደገፍ እየተላለቁ መፍረስን መደገፍና መተባበር ነው። በአጠቃላይ- ከፊታችን አፍጥጦ የመጣው ሌላ ዙር ጦርነት ለይቶለት ከፈነዳ በየትኛውም ምክኒያት አገዛዙን ደግፋችሁ የቆማችሁ ዜጐች ጸጸታችሁ የዕድሜ ልክ፣ ተጠያቂነታችሁም ከህሊና አልፎ የትውልድና የታሪክ እንደሚሆን ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም።
ደራሲ በዓሉ ግርማም ሆነ እነ ጀነራል ፋንታ በላይ ውድ ህይዎታቸውን ያጡበት ዓላማ መነሻውም ሆነ መድረሻው የስልጣን ጥያቄ አልነበረም። ይልቁንም በጦርነት ተስፋ ከመቁረጥ የመነጨና “ሌላ ሰላማዊ አማራጭ ይፈለግ” የሚል አዋጭ መፍትሄ የመሻት ሙከራ ነበር። ሰሚ ባለማግኘታቸው እነሱ የሰጉት እንጅ የተመኙት አልሆነም። ከመቃብራቸው ቀና ብለው የዛሬው የኛ ትውልድ እነሱ የሞቱለትን ስጋት በብዙ እጥፍ አባብሶ የቀጠለበት መሆኑን ቢመለከቱ ምን ያህል በትዝብትና በንቀት ባዩን ነበር።
የሆነ ሆኖ፣ እነሱ ላመኑበት በመሞት የሀገርና የህዝብ ህልውና ጉዳይ ምን ያህል ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ ታላቅ አጀንዳ እንደሆነ ብቸኛ ህይዎታቸውን ገብረው ማሳየት በመቻል ዕድለኞችና ባለ ታሪክ ሰማዕታት ሆነዋል።
የሰጉት መሆኑ ባለመቅረቱ ደግሞ ዕድለ-ቢሶችም ናቸው። እኔ ግን ስጋቴን የመግለፅ እንጅ እንደነሱ ላመንኩበት የመኖርና የመሞት ዕድልን አላገኘሁም። ያን ዕድል የተነፈግሁ ሀገርና ዜግነትን የተቀማሁ ከርታታ ስደተኛ ነኝና—።
ኦሮማይ!! ጦርነት ይብቃ!፣ ሰላም ይምጣ!
ልደቱ አያሌው
ሚያዚያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም




