ሚድያችን በከተማ አስተዳደሩ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ውስጥ ያለውን ሰፊ የሙስና ሰንሰለት ማጋለጡን ተከትሎ ተቋሙ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ በኦላይን ሊያደርግ መሆኑን ዛሬ አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን የዛሬ ሳምንት ህዳር 3/2018 ዓ.ም ባወጣው አንድ ሰፊ ዘገባ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሙሰኛ ሰራተኞች ለጤና ባለሙያዎች ምዝገባና የሙያ ስራ ፈቃድ ለመስጠት እና ለማደስ ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ጉቦ እየተቀበሉ መሆኑን አጋልጦ ነበር (የዜናው ሊንክ: https://tinyurl.com/93bbkpwx)
በዚህ ዘገባ ላይ እንደተመላከተው አገልግሎት ፈላጊዎች ሁሉንም የሚጠየቀውን አሟልተው በቀጠሯቸው መሰረት አራት ኪሎ ወደሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት ባላስልጣን በሚሄዱበት ወቅት የተለያዩ ምክንያት በመጥቀስ የተመደቡት ባለሙያዎች የጉቦ ገንዘብ እየተቀበሉ ቆይተዋል።
ይህ ዘገባ በወጣ በሳምንቱ ዛሬ ተቋሙ በፌስቡክ ገፁ እንዳስታወቀው ከህዳር 30 /2018 ዓ.ም ጀምሮ የጤና ባለሞያዎች አዲስ እና እድሳት የብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ኦላይን በማድረግ ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ እንዲሁም ዲግሪ እና ከዛ በታች ያለ የትምህርት ደረጃዎች ያላቸው የጤና ባለሞያዎች በቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ኦላይን በማመልከት እንዲገለገሉ የማድረግ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመሩን አስታውቋል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ በተቋሙ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ በተለቀቀ መረጃ ላይ እንዳሉት "በከተማችን በየወቅቱ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ባለሙያዎች ቁጥር በርካታ በመሆኑና በአንድ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ብቻ በማስተናገድ ማርካት የማይቻል በመሆኑ የጤና ባለሙያ የሙያ ምዝገባ፣ ፈቃድና ዕድሳት ስራ ካስኬድ በማድረግ ዲግሪና ከዛ በታች ያሉ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የጤና ባለሞያዎች በቅርንጫፍ ባሉ የባለስልጣኑ ፅ/ቤቶች ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ከዲግሪ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው የጤና ባለሞያዎች በዋናው ባለስልጣን መስሪያ ቤት ስር በኦላይን አገልግሎት ለመስጠት ተወስኗል" ብለዋል።
ዋና ስራ አስኪያጇ አክለውም የጤና ሙያ ምዝገባ እና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ በተዋረድ ካስኬድ እና ሙሉ በሙሉ ኦንላይን በማድረግ ተገልጋዩን በያለበት ለመገልገል የሚያስችል ዕድል የሚያጎናፅፍ መሆኑ፣ የተገልጋዩ ፍላጎትና የስራ ባህሪ ማለትም የጤና ባለሙያው የእለት ተዕለት ስራው ከሰው መርዳት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ግዜውን አጣጥሞ በያለበት መገልገል እንዲስችል፣ ለብልሹ አሰራር ተጋላጭነትን የሚቀንስ እና ፈጣን አገልግሎት ለማሳለጥ የሚያስችል ብሎም ግልፅና ለተጠያቂነት የሚያመች ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ስርዓት ለመዘርጋት ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።
በዚህም መሰረት የቴክኖሎጂ ቴክኒካል ስልጠና፣ የአሰራር ማንዋሎች ማዘጋጀት፣ የግብአት ሟሟላት የመሳሰሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ከህዳር 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር ለመግባት እቅድ መያዙን ገልጸው የሞያ ፍቃድ አዲስና እድሳት የሚያደርጉ የጤና ባለሞያዎች ባሉበት በመሆን አገልግሎቱን በኦላይን ሲስተም በማመልከት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ሚድያችን ባወጣው ዘገባ ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ተገልጋዮች "ወደሚመለከተው የተቋሙ ኃላፊ ስንሄድ ስልካቸውን ይሰጡን እና ደውል ዛሬ በጣም ስራ አለኝ በማለት ይመልሱናል። በተደጋጋሚ ወደ ቢሮና በግል ስልካቸው በመደውል የተባልነውን ስናስረዳ እና ምሳ ሰዓት በመቅጠር አብረን እየሄድን እናውራ በማለት ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የስራ ማስኪጃ እንጠየቃለን" በማለት አስረድተው ነበር።
"በዚህም መሰረት እንደ ነገሮች አረዳዳችን ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እንድንከፍል እና ምንም አይነት ስልክ እንዳንደውል ብሩን ማስገባት ከፈለግን ግን አካውንት ይሰጠናል። ብር አስገብተን ማስገባታችንን በአካውንቱ የገባለት ሰውዬ ገብቷል ሲል የሙያ ፍቃዱ በሰከንድ ውስጥ ይሰጠናል። ነገር ግን ይህንን እንቢ የሚሉትን ባለሙያዎች ከ 6 ወር እስክ 1 አመት ኢንተርንሺፕ መስራት አለባችሁ በሚል ደብዳቤ የጽፋሉ" በማለት ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ በፎርጅድ የትምህርት ማስረጃ ማለትም የመጀመሪያ ዲግሪ ኖሯቸው እና ሁለተኛ ዲግሪ ለሌላቸውና ባለሙያዎች አግባብ ያለው ክፍያ ለሚከፍሉ የተለያዩ የሙያ እድገት ለምሳሌ Expert እና Consultant የሚባሉ ደረጃዎችም እየተሰጡ እንደሚገኝም በዘገባው ላይ ተጠቅሶ ነበር።
-መሠረት ሚድያ-




