የሰሞኑን የፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ንግግርን ተከትሎ ኢትዮጵያ ግድቡን በሀገር ውስጥ አቅም እየገነባች መሆኑን በዛሬው ዕለት አስታወቀች
(መሠረት ሚድያ)- የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ከሰሞኑ በተከታታይ ሶስት ግዜ ሀገራቸው የህዳሴ ግድብን ፋይናንስ እንዳደረገች ሲናገሩ ተደምጠው ነበር።
ፕሬዝደንቱ በዚህ ከግብፅ የወገነ ንግግራቸው የህዳሴ ግድብ ወደ ናይል ወንዝ የሚገባውን ውሀ እየዘጋው ነው እንዲሁም የናይል ወንዝ ለግብፅ ብቸኛው የህይወት ምንጭ ነው በማለት ተናግረዋል።
ለዚህ የፕሬዝደንቱ ምላሽ እስካሁን በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ውጭ ጉዳይ ቢሮ የተሰጠ ምላሽ ባይኖርም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በዛሬው እለት ሚድያዎችን ጠርቶ በሰጠው መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ አቅም መገንባቷን አፅንኦት ሰጥቶ ተናግሯል።
ፅህፈት ቤቱ ግድቡ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ወጪ እንደተገነባ ያረጋገጠ ሲሆን በያዝነው አመት ብቻ ከ1.7 ቢልየን ብር በላይ ለግድቡ ማሰባሰቡን መናገሩን ካፒታል ዘግቧል።
ከግንባታው መጀመር ጀምሮ በአጠቃላይ ከ23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ከህዝብ የተሰበሰበ ሲሆን ከ84.4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የጉልበትና የተፋሰስ ስራዎች ተከናውነዋል ሲል ፅህፈት ቤቱ አክሏል።
ይሄ ማረጋገጫ ሊመጣ የቻለው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች የሚል ክስ ለሶስተኛ ጊዜ መናገራቸውን ተከትሎ ቢሆንም አሁን የሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ዲፕሎማቶች ዝምታን መምረጣቸው በአንዳንዶች ዘንድ የአሜሪካ ንግግር 'እውነት ይሆን እንዴ?' የሚል ጥያቄን አጭሯል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የፕሬዝደንት ትረምፕ ንግግርን በማጣጣል ግድቡ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሲደገፍ መቆየቱን አጽንኦት ሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቁንና በመጪው መስከረም ወር እንደሚመረቅ ገልጸው፣ ግብፅንና ሱዳንን በይፋ መጋበዛቸው ይታወሳል።
ግብፅና ሱዳን በበኩላቸው፣ የውሃ ድርሻቸውን ይጎዳል በሚል ስጋት ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትገባ ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
ፕሬዝደንት ትረምፕ በሰሞንኛው ንግግራቸው ላይ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ጥቅም፣ በኢትዮጵያ መሬት ላይ እየተገነባ መሆኑን እንዲሁም በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን መዋጮ የተሰራ መሆኑን አልጠቀሱም።
ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ገንዘብ በማግኘት በአባይ ወንዝ ላይ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ለመገንባት ለበርካታ አመታት ብዙ ሙከራ አድርጋ የነበረ ቢሆንም በግብፅ ተፅእኖ ምክንያት አለመሳካቱ ይታወቃል።
በዚህም ምክንያት የዛሬ 13 አመት የህዳሴ ግድብን በራስ ወጪ ለመገንባት እቅድ ተነድፎ እንቅስቃሴ መጀመሩን መንግስት ገልፆ ነበር።
ለማሳያነት ከሀገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭ እና ከዜጎች መዋጮ እስከ 450 ሚልዮን ዶላር፣ የባለሀብቶች ተሳትፎ 88 ሚልዮን ዶላር ገደማ፣ የቻይና ብድር 2.2 ቢልዮን ዶላር እንዲሁም ዋናው ከመንግስት ወጪ 5 ቢልዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ፕሬዝደንቱ በርዋንዳ እና ኮንጎ፣ በህንድ እና ፓኪስታን፣ በሰርቢያ እና በኮሶቮ እንዲሁም በግብፅ እና በኢትዮጵያ መሀል ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ማረጋቸውን ጠቅሰው ለዚህም የኖቤል የሰላም ሽልማት ቢገባቸውም እንዳልተሰጣቸው ከዚህ በፊት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
መረጃን ከመሠረት!



