"ከባህር ዳር የተነሱ የኢትዮጵያ እና የኤምሬትሶች ድሮኖች ካርቱም ላይ ጥቃት ፈፅመዋል"- ሱዳን "ሱዳን የፀረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች መሰባሰቢያ ሆናለች"- ኢትዮጵያ
(መሠረት ሚድያ)- በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እየተበላሸ የመጣ ሲሆን፣ ትናንት ሰኞ በካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት ተከትሎ የቃላት ጦርነቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሯል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሂዲን ሳሌም እና የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ አሲም አዋድ አብድ አል-ዋሃብ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢትዮጵያ በጥቃቱ በቀጥታ እጃቸው እንዳለበት በይፋ ከሰዋል።
የሱዳን ባለስልጣናት ጥቃቱን የፈጸሙት ድሮኖች መነሻቸውን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ማድረጋቸውን የሚያረጋግጥ "ተጨባጭ የቴክኒክ መረጃ" እንዳላቸው በመግለጽ፣ በተለይም የኤምሬትስ ንብረት የሆነና S88 የሚል መለያ ቁጥር ያለው ድሮን በኢትዮጵያ የአየር ክልል በኩል አልፎ ጥቃቱን መፈጸሙን አስታውቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ ሱዳን በአዲስ አበባ የሚገኘውን አምባሳደሯን ለምክክር የጠራች ሲሆን፣ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ እስከ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ሊያደርስ የሚችል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን በማስጠንቀቅ ዛቻ ሰንዝራለች።
ለዚህ ብርቱ ክስ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሱዳን መንግስት ያቀረበውን ወቀሳ "መሰረተ ቢስ እና ሃሰተኛ" በማለት ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ በመግለጫዋ ላይ እንደጠቆመችው የሱዳን ጦር ኃይሎች እያቀረቡ ያሉት ክስ የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎች ፍላጎትና ግፊት የሚከናወን እንጂ ተጨባጭነት የሌለው መሆኑን ገልጻለች።
ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳንን በምላሹ የከሰሰ ሲሆን ሱዳን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ "የህወሃት ቅጥረኞችን" እያሰለጠነች፣ የገንዘብና የትጥቅ ድጋፍ እያደረገች እንዲሁም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረች መሆኑን በዝርዝር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ወንድማማችነት ስትል በትዕግስት ጉዳዩን ይዛ መቆየቷን የገለጸው መግለጫው፣ ሱዳን ግን የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መናኸሪያ በመሆን የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት እየጣሰች እንደሆነ ወቅሷል።
በአሁኑ ወቅት በካርቱም እና በአዲስ አበባ መካከል ያለው ግንኙነት አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርስ የጥቃት እና የሉዓላዊነት መጣስ ክሶችን በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ።
ሱዳን የአየር ጥቃቱን እንደ ከባድ የጦርነት ትንኮሳ ስትቆጥረው ኢትዮጵያ በበኩሏ የሱዳን ባለስልጣናት ትኩረትን ከአገር ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ሌላ የውጭ ጠላት የመፍጠር ስትራቴጂ እየተከተሉ እንደሆነ ትሞግታለች።
| መሠረት ሚድያ |



