(መሠረት ሚድያ)- በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አነጋጋሪ እና አሳሳቢ ድርጊት መፈጸሙ ተሰምቷል። በትምህርት ቤቱ አመራር ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ተያያዥ አጋጣሚዎች የብዙዎችን ትኩረት የሳቡ ሲሆን ጉዳዩ በአሁኑ ወቅት በሕግ አስከባሪ አካላት እና በስራ ኃላፊዎች ዘንድ ትኩረት አግኝቶ ማጣራት እየተደረገበት ይገኛል።
የችግሩን ስፋት እና የተፈጸመውን ክስተት ዝርዝር መረጃ ለማወቅ ከዚህ በታች ያለውን ሙሉ ዘገባ ያንብቡ።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የድላችን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ጉዲና በተማሪዎች፣ በወላጆች እና ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ቢሯቸው በሚመጡ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጾታዊ ትንኮሳ ሲፈጽሙ እንደነበር የሚገልጹ መረጃዎች ደርሰውናል።
ተጎጂዎች እና ቅሬታ አቅራቢዎች ስለ አቶ በቀለ ድርጊት ለክፍለ ከተማው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአቶ ብሩክ እንዲሁም ለከተማው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአቶ ዘላለም አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የእርምት እርምጃ ሳይወሰድ እና ሰሚ በማጣት መቆየታቸው ተገልጿል።
ይባስ ብሎ ርዕሰ መምህሩ አቤቱታ ያቀረቡ ተማሪዎችን የመቅጣት እና ወላጆችን የማስፈራራት ድርጊት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
"የነገሩ መባባስ ይፋ የሆነው ባለፈው ሳምንት አንዲት እናት ልጃቸውን ለማስመዝገብ ወደ ትምህርት ቤቱ በሄዱበት ወቅት ነው" በማለት ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ አንድ ግለሰብ ናቸው።
አክለውም "ርዕሰ መምህሩ የተለመደ ድርጊታቸውን ለመፈጸም የቢሮውን በር ቆልፈው ጥቃት ሊያደርሱ ሲሉ ተጎጂዋ ባሰማችው የይድረሱልኝ ጩኸት በአካባቢው የነበሩ ባለጉዳዮች በበሩ በኩል ደርሰው ሊያድኗት ችለዋል። በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ ግብግብ የተጎጂዋ ፊት የተቦጨረ ሲሆን ነጠላዋም ተቀዳዷል" በማለት አስረድተዋል።
መሠረት ሚድያ የጉዳዩን እውነተኝነት ከሁለት መምህራን እንዲሁም ከሶስት ተማሪዎች አረጋግጧል።
ድርጊቱን ተከትሎ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች በትግል አቶ በቀለ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲወሰዱ መደረጋቸው ታውቋል።
አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የትምህርት ቤቱ መምህር ለመሠረት ሚዲያ እንደገለጸው አቶ በቀለ ከሦስት ዓመት በፊት ኮልፋ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ተዛውረው ወደ ድላችን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር የተዛወሩት። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሲፈጸም የነበረው ጾታዊ ትንኮሳ እውነት መሆኑን አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ ርዕሰ መምህሩ ከበላይ አካላት ጋር አላቸው በሚባል የጥቅም እና የቅርብ ቁርኝት ምክንያት የሕግ ሂደቱ እንዳይዛባ እና ፍርደ-ገምድል እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ምንጮች ያስረዳሉ።
በመሆኑም በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም እና ፍትሕ እንዲነግስ የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ እና የሕዝብ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቀርቧል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት በግቢው ውስጥ የሚገኙ መምህራን፣ የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች እና የቀድሞ ተማሪዎች ተጨማሪ መረጃዎችን በመስጠት እውነቱ ይበልጥ ይፋ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
| መሠረት ሚድያ |





ቅፅል ስሙ እራሱ ባልታዘር ነው
ኢትዮጵያዊ ባልተዛር