ከሶማሊያ እና ኤርትራ ስደተኞች ከፍተኛ ገንዘብ በህገወጥ መልኩ በመቀበል የስደተኛ ዶክመንት እየተሰጠ መሆኑ ተጠቆመ
(መሠረት ሚድያ)- የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ሊነሳ የሚችለዉን የደህንነት ስጋት ለመቀነስ ያስችል ዘንድ የጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያቀርቡትን የእዉቅና ጥያቄ የጸጥታ ማጣራት (security screening) እና የዜግነት ማጣራት (ationality screening) በማከናወን ምዝገባ ያካሂዳል።
ይህም ምዝገባ የሃገርን ጸጥታ ከመጠበቅ አንጻር ጉልህ ሚና ያለዉ ነው ተብሎ ይታመናል።
በዚህም ከኤርትራ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል በሚገኘዉ የእንዳባጉና ማጣሪያ ጣቢያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አባላትና የሃገር መከላከያ ሠራዊት የመረጃ ሠራተኞች በሚያደርጉት ማጣራት የስደተኝነት እዉቅና ሲሰጥ ከ15 ዓመታት በላይ ሲሰራበት ቆይቷል።
ይሁንና የዛሬ ሰባት አመት ገደማ የመንግስት ለውጥ ከተደረገ በሗላ የአዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባና ቅበላ እንዲቆም ተደርጓል።
ከዚህ ግዜ በሗላ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ ምዝገባዎች በስደተኝነት ተመዝግበዉ ከሚኖሩ ስደተኞች የተወለዱ ህጻናትን ብቻ እንዲመዘገቡ የሚደረግ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ማንነታቸዉ በግልፅ ማይታወው በተለይም የኤርትራ እና የሱማሌ ዜግነት አላቸዉ የተባሉ ግለሰቦች የህፃናት የምዝገባ መለያ ቁጥር እየተሰጣቸው መሆኑን መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ይህ ሲሆን ደግሞ በተቋሙ ለሚገኙ አመራሮች እና ሠራተኞች ከፍተኛ መጠን ያለዉ የገንዘብ ክፍያ በመፈጸም በተለይ በአዲስ አበባና በጅግጅጋ ከተሞች በስፋት እየተመዘገቡ መሆኑ ታውቋል።
በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለረጅም አመታት በተለያየ የሃላፊነት ቦታ የሠሩ ሠራተኞች ለመሠረት ሚድያ እንደሚናገሩት በተቋሙ አመራሮች በስደተኞች ምዝገባና በሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራት ዙርያ ላለፉት ስድስት ወራት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለፀረ- ሙስና ኮሚሽን፣ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም ለፍህትህ ሚኒስትር በርካታ አቤቱታዎችን አቅርበው ምላሽ አላገኙም።
"በማስረጃና በመረጃ የቀረቡ ጥቆማዎችን የተቋሙ አመራር ከላይ እስከታች በዘረጋዉ ኔትወርክ ምክንያት የተጀመሩ የምርመራ ስራዎችን ተከታትሎ እንዲጓተቱ በማድረግ ብሎም እንዲቋረጡ እስከ ማስደረግ ደርሰዋል" በማለት ተናግረዋል።
ለኤርትራውያን አዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያቀርቡትን የስደተኝነት እወቅና (Refugee Status Determination) ሂደት ሳያልፉ እና በዚህ ሂደት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተሳትፎ ሳይኖርበት ወይንም በአዋጅ ቁጥር 1110/2011 ላይ በአንቀጽ 18 በተራ ቁጥር 2 የተገለጸዉን የተባበሩት መንግታት ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽን በታዛቢነት እንዲሳተፍ የተገለጸዉን የህግ አንቀጽ ባላሟላ ሁኔታ ምዝገባ የተካሄደዉ እንደሚገኝ እነዚህ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ጥያቄዎች በማንሳት ላይ ይገኛል፡፡
በተያያዘም በአዲስ አበባ ደረጃ የኤርትራ ጥገኝነት ጠያቂዎች ምንም አይነት ምዝገባ ተካሂዶ እንደማያዉቅ እየታወቀ የስደተኝነት እዉቅና ለማግኘት የሚጠይቁ ኤርትራዊያንን ከዚህ በፊት የስደተኝነት እዉቅና ካገኙ ስደተኞች የተወለዱ ህጻናትን ለመመዝገብ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የሚሰጥን የስደተኞች መለያ ቁጥር (በ 427) የሚጀምር ቁጥር ለአዲስ አዋቂ ለሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች አየተሰጠ ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል፣ ሊሆን የሚገባዉ ግን (በ130) የሚጀምር መለያ ቁጥር መሆን ነበረበት፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በጅግጅጋ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ለረጅም ጊዜ ያልተመዘገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች አሉ በሚል በነሃሴ 2016 ዓ.ም እና በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም በጅግጅጋ የተካሄደዉ የአዲስ ስደተኞች ምዝገባ በክፍያ ሲከናወን ቆይቶዋል፡፡
ይህም አለም አቀፍ ህግ የሆነዉን በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽንም ሆነ በአጋር አካላት የሚቀርቡ አገልግሎቶች ከክፍያ ነጻ ይቀርባሉ የሚለዉን መርህ የጣሰ መሆኑ ታውቋል።
ይህ ህገ-ወጥና ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ በማስከፈል የሚፈጸመዉን የኤርትራዊያንና ሶማሊያዊያን ስደተኞች ምዝገባና ሌሎች በተቋሙ ዉስጥ የሚፈፀሙ ከፍተኛ የሙስና ወንጀሎች ጥቆማ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን የቀረበ ሲሆን የቀረቡለትን ጥቆማ በመረጃና በማስረጃ በማስደገፍ ጉዳዩን ለፌደራል ወንጀል ምርመራ ቀርቦ ነበር።
የፌደራል ወንጀል ምርመራ የቀረበለትን የምርመራ ጥያቄ በማጠናከር ምርመራዉን ለመጀመር ለፍትህ ሚኒስትር ጥያቄ በማቅረብ የምርመራ ስራዉን የጀመረ ሲሆን በምርመራ ወቅት የፌደራል ፖሊስ ያከናወናቸዉ ሥራዎች የዉስጥ ኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ በኦዲት ስራዉ የተሳተፉ የኦዲት ሪፖርቱ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጫ አግኝቷል።
በዚህም ሪፖርቱ ሰፊ ይዘት ያለዉ በመሆኑ ወደ ወንጀል መዝገብ በእጅ ፅሁፍ መገልበጥ ስላለበት ረጅም ጊዜ የወሰደ ሲሆን ከተጠናቀቀ በኃላ ኦዲተሮች በሪፖርቱ ላይ እንዲፈርሙ ተደርጓል።
በአጠቃላይ በስደተኞች ስም የመጣን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በበላይ አመራሩ ምዝበራ የተፈጸመበት ነዉ፤ ከዚህ በተጨማሪም በህገ -ወጥ የተመዘገቡ እንደ ማሳያ የቀረቡ የተመዘገቡ ስደተኞችን መነሻ በማድረግ የፌደራል ፖሊስ ለተቋሙ በደብዳቤ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን በጥያቄዉም ከግንቦት 1/2016 እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘዉ የተቋሙ ቢሮ የተመዘገቡ ስደተኞችና ከነሃሴ 1/2016 - መስከረም 30/2017 በጅግጅጋ በሚገኘዉ ቢሮ የተመዘገቡ ዝርዝር እንዲላክለት ጥያቄ ኡቅርቧል።
ከተቋሙ ያገኘዉ ምላሽ ከዳታ ቤዝ ፕሪንት/Print/ ማድረግ ስለማይቻል ማቅረብ አልችልም የሚል የተሳሳተ የሆነ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ምላሽ ቅጥፈት እንደሆነ በድጋሚ ከጥቆማ ሰጭዎችና ከጸረ- ሙስና ኮሚሽን ጥያቄ ቢቀርብም በፍትህ ሚኒስት የሚሰሩና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ላይ የሚገኙት አቶ ተስፋየ ዳባ በተባሉ የመንግስት የስራ ሃላፊ የምርመራ ስራዉ እንዲጓተት ብሎም እንዲቆም ለመርማሪዎች የተለያየ ምክንያት በመስጠት የተጀመሩ የምርመራ ስራዎችን ለጊዜዉም ቢሆን እንዲቆም ማድረጋቸው ታውቋል።
በነዚህ ምርመራዎች ወቅት በተደረገ ማጣራት በአንድ አካዉንት ብቻ ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ከስደተኞች ምዝገባ ብቻ በህገ-ወጥ መልኩ የተሰበሰበ ገንዘብ መገኘቱ ታውቋል፣ በዚህም አንድ ስደተኛ የስደተኝነት እዉቅና ለማግኘት ከ400 ሺህ እስከ 600 ሺህ ንር ክፍያ ይፈጽም እንደነበር ተረጋግጧል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1263/2021 ተጠሪነቱ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሆኖ የተቋቋመ ተቋም ነዉ፡፡
ተቋሙ በተለያዩ ስያሜዎች ከ50 ዓመት ያላነሰ እድሜ ያለዉ ሲሆን በዋናነት በኢትዮጵያ ዉስጥ ተጠልለዉ ለሚገኙ የተለያዩ ሃገራት ስደተኞችን ተቀብሎ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ በማስተባበር ለስደተኞች አስፈላጊዉን ሰብዓዊና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያኙ እንዲሁም ደህንነታቸዉን የመጠበቅ ተግባር ማከናወን ነዉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከ 1.1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የጎረቤት ሃገራት ዜጎች ተቀብሎ በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
ተቋሙ አመታዊ በጀቱን የሚያገኘዉ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (United Nation High Commission for Refugees) ሲሆን በጀቱ የሠራተኛ ደምወዝና የተለያዩ የሥራ ማስኬጃን ያጠቃልላል፤ ከዚህ በተጨማሪም የተሽከርካሪና ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎች ያቀርባል፡፡
በዚህ ዙርያ ምላሽ ለማግኘት ሚድያችን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ወ/ሮ ጠይባ ሀሰንን መረጃ ጠይቆ ነበር።
ይሁንና ዋና ዳይሬክተሯ "ማንም ሚድያ ወደ ቢሯችን በመምጣት መረጃ ማግኘት ይችላል" ካሉ በኋላ በስልክ መረጃ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
Photo: UNHCR መረጃን
ከመሠረት!





