በአርሲ ዞን ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ በአጨዳ ላይ የነበሩ ከ15 በላይ ገበሬዎች ታፍነው ተወሰዱ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ የበርካታ ንፁሀን ዜጎችን ሞት ያስተናገደው የአርሲ ዞን አሁን ደግሞ የበርካታ ሰዎች መታገቻ መሆኑም ምንጮቻችን እየጠቆሙ ይገኛሉ።
በትናንትናው ዕለት በአርሲ ዞን ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ በአጨዳ ላይ የነበሩ ከ15 በላይ ገበሬዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚድያችን ተናግረዋል።
ከታፋኞቹ መሀል ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ ይገኝበታል ተብሏል። የአሁኑ እገታ የተፈፀመው በአርሲ ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ፣ መጭቱ ለማን ቀበሌ ልዩ ስሙ በቀቅሳ የሚባል ቦታ መሆኑ ታውቋል።
"አፋኞቹ ኦነግ ሸኔዎች ናቸው ይባላል፣ እኛ ግን ማረጋገጥ አንችልም። እስካሁን በሕይት ላይ የደረሰ አደጋ የተወቀ ነገር የለም" በማለት ምንጮቹ ጠቁመዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በተፈፀሙ አራት ተከታታይ ጥቃቶች 28 ሰላማዊ ሰዎች ግድያ እንደተፈፀመባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በሆንቆሌ ዋቤ ወረዳ በቀቅሳ ቀበሌ ጥቅምት 18 ለ19 አጥቢያ ከምሽቱ 4፡00 ላይ አምስት ምእመናን በታጣቂዎች መገደላቸው ተዘግቦ ነበር።
በተመሳሳይ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ከለሊቱ 4 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ ሄላ ዘባባ ቀበሌ አርሴማ አጥቢያ የሚኖሩ ምእመናን በታጠቁ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱ መገደላቸው እና አራቱ ደግሞ መታገታቸው ተገልጿል።
በሶስተኛነት በአርሲ ሀገረ ስብከት ጉና ወረዳ በሚገኘ ኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ 14 ምዕመናን ከለሊቱ 6 ሰዓት አካባቢ በዕለተ ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ለ14 አጥቢያ ከተኙበት ከቤታቸው አስወጥተው የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን ስድስቱ ከመገደላቸው ከአንድ ቀን በፈት ቀድመው ታፍነው ተወስደው ነበር ተብሏል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2016 ዓ.ም መስከረም 02 ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያለማቋረጥ በወረዳው ከ115 በላይ ምእመናን የተገደሉ ሲሆን 27 ምዕመናን ደግሞ አሁንም ድረስ ታግተው ያሉበት እንደማይታወቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
-መሠረት ሚድያ-



