ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ 'ዶ/ር ደቦል' በ15 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተፈታ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ ሲያሰሙት የነበረውን ድምፅ እና ሲያቀርቡት የነበረውን የመብት እና የጥቅም ጥያቄ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በማስተጋባት የሚታወቀው 'ዶ/ር ደቦል' ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
የባህር ዳር ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባልደረባ የሆናው ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ በዛሬው እለት በዋስ መፈታቱን መሠረት ሚድያ አረጋግጧል።
ዶ/ር ዳንኤል የ 'ዶክተር ደቦል' የፌስቡክ ገፅ መስራች፣ የደቦል የቀዶ ጥገና የተማሪዎች መርጃ መፅሐፍ አዘጋጅ፣ የደቦል የክሊኒክ አከፋፈት መርጃ መጽሐፍ አዘጋጅ እንዲሁም የ MAC ኢትዮጵያ ተባባሪ መስራች እና የጤና ባለሙያዎች መብት እና ህልውና ተከራካሪ በመሆኑ በስፋት ይታወቃል።
የዶ/ር ዳንኤልን መፈታት ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ይህንን 'አዎንታዊ' እርምጃ እያበረታታ ማንኛውም የጤና ባለሙያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብቱን በመጠየቁ ወይም ለጤና ስርዓት ማሻሻያዎች በመሟገቱ ያለ ፍትህ የሚደረግ እስራትን አጥብቀን እያወገዝን ነው ብሏል።
"የዶ/ር ደቦል መታሰር በሙያችን ውስጥ ለፍትህ የሚታገሉ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ጭቆና አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ለእሱ እና ለሌሎች የታሰሩ የጤና ባለሙያዎች ድምፃቸውን ላሰሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፣ ለእስረኛ ቤተሰቦች እና ጓደኞቹ ፣ ለሥራ ባልደረቦቹ ፣ ለመገናኛ ብዙሃን ፣ ለጋዜጠኞች እና በእስር ላይ በነበረበት ወቅት እሱን በመጎብኘት እና ለነፃነቱ ጥሪውን በማጉላት ከእርሱ ጋር አብረው ለተሰለፉ ሁሉ ጥልቅ ምስጋናችንን እናቀርባለን" ብሏል ማህበሩ በመግለጫው።
ማህበሩ አክሎም "ቆራጥነታችሁ እና አንድነታችሁ ለዚህ ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። አቋማችን ግልፅ ነው: መሰረታዊ መብቶችን መጠየቅ ወንጀል አይደለም፣ ለጤና ባለሞያዎች የህልውና ወሳኝ ጉዳዮች ወቅታዊ እና ተጨባጭ መፍትሄዎችን ይገባቸዋል፣ እነዚህ ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መልስ እስከሚሟሉ ድረስ የጋራ ትግላችን ይቀጥላል" ብሏል።
ዶ/ር ዳንኤል ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት 'የጤና ባለሞያውን በማንቃት፣ በመቀስቀስ፣ በማደራጀት እና የስራ ማቆም አድማ በማድረግ የሰው ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ' የሚል ክስ እንደተመሰረተበት መሠረት ሚድያ መዘገቡ ይታወሳል።
መረጃን ከመሠረት!



