በአሰራሩ ዙርያ ሚድያችን ጥያቄ አንስቶበት የነበረው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በትናንትናው እለት 14 ከፍተኛ አመራሮቹን ከስራ አሰናበተ
(መሠረት ሚድያ)- "የቁልቁለት ጉዞ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን" በሚል ርዕስ ሚድያችን ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም የህዝብ አስተያየት የሆነ መረጃ ለተከታታዮቹ ማቅረቡ ይታወሳል (ሊንክ: https://t.me/meseretmedia/883)
የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመባል የሚታወቁትን ከ30 በላይ የንግድ ተቋማትን በአንድ እናት ኩባንያ (ሆልዲንግ ኩባንያ) ስር በማሰባሰብ የሪፎርም ስራ መስራት ተጀመረ ከተባለ አመታት ማለፉ ተነስቶ ነበር።
መንግስታዊውን ኢቲቪን ጨምሮ በርካታ ሚድያዎች በለውጥ ጉዞ ላይ ስለመሆኑ ደጋግመው የመሰከሩለት የኢትዮጵያ ኮንስትራኩሾን ስራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ) በተቃራኒው ወደ ውድቀት እየተንደረደረ ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች በተለያዩ የሶሻል ሚዲያ ገጾች ጭምር ቢሰራጩም ከቁብ የቆጠራቸው እንዳልነበር ይህ ቀድመን ያጋራነው መረጃ ያሳያል።
ይህን ተከትሎ የቀድሞው የኢኮስኮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ከስራቸው ተነስተው በአቶ ሮቤል ፀጋዬ ተተክተዋል። አሁን የደረሰን አዲስ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ተቋሙ በትናንትናው እለት 14 ከፍተኛ አመራሮቹን ከስራ አሰናብቷል።
ኮርፖሬሽኑ እርምጃውን የወሰዱት የአመራር ድክመትን ለማስቀረት እና ግልፅነትን ለማስፈን እንደሆነ በትናንትናው እለት የፃፉትን ደብዳቤ ተመልክተናል።
በአቶ ሮቤል የተፃፈው ይህ ደብዳቤ ተቋሙ ፕሮጀክቶችን ሰርቶ የመጨረስ አቅሙ አነስተኛ እንደነበር፣ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች የተቋሙን ፋይናንስ እንዳዳከመ እንዲሁም ተጠያቂነት ያለው አሰራር በተቋሙ እንዳልነበር ያነሳል።
በዚህም ምክንያት የኢኮስኮ ምክትል ስራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ 14 ሰዎች በአስቸኳይ ከስራ እንዲነሱ ተደርገዋል።
ከስራቸው የተነሱት ከፍተኛ አመራሮች አሰፋ ከሲቶ፣ በእምነት ጋሻው፣ ዶ/ር ቤዛዊት ግርማ፣ ኢሳያስ አንዳርጌ፣ ፍፁም ታምሩ፣ ሳሙኤል አማረ፣ ሸዋንግዛው ተስፋዬ፣ ሱራፌል አባይነህ፣ ታደለ ፉሌ፣ ዋቅጅራ ይልማ፣ ወገን ሰለሞን፣ ዮሀንስ አየለ፣ ዘሪሁን መኩሪያ እና ዘይነባ ኡመር መሆናቸው ታውቋል።
ኢኮስኮ ባለፉት 3 ዓመታት በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻግሮ ጭምር ከጅቡቲ መንግሥት ኮንትራት ወስዶ ሲሰራቸው ከነበሩ ፕሮጀክቶች መካከል ከደርዘን በላይ የሚሆኑትን በገባው ውል መሠረት አጠናቆ ለማስረከብ ባለመቻሉ ውሉ ተቁዋርጦ ለደረሰው ጉዳትም ኢንሹራንስ ካሳ እንዲከፍል በመጠየቅ ላይ እንደሚገኝ ሚድያችን መረጃ ማቅረቡ ይታወሳል።
በዚህ ረገድ ለአብነት ከሚጠቀሱ ፕሮጀክቶች መካክል የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት አንዱና ዋነኛው ነው። ኢኮስኮ ለአመታት የዚህን የግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ቢያጓትትም በውሉ መሰረት ለመፈጸም ባለመቻሉ በቀድሞዋ የመስኖ ሚኒስተር ኢ/ር አይሻ መሀመድ በቀን 15/05/2024 በቁጥር 01/4183 በተጻፈ ደብዳቤ ዉሉ ተቁዋርጦ ፕሮጀክቱ ለሌላ ኮንትራክተር ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡
ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ተረክቦ ይሰራቸው ከነበሩ 6 የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ባለስልጣኑ በቀን26/07/2024 በቁጥር 644/Dir/G/2024 በፃፈው ደብዳቤ ኮርፖሬሽኑ በፈጠረው ችግር ምክንያት ሶስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውል መቋረጡን ጠቁሞ በተቀሩት ላይም ለመወያየት ለኮርፖሬሽኑ ጥሪ አድርጎ ነበር፡፡
ይህ ከሆነ ከወራት በሗላ የተቀሩትንም ሶስት መንገዶች በውሉ መሰረት ለመፈፀም ባለመቻሉ ውሉ የተቁዋረጠ ሲሆን በድምሩ በአዲስ አበባ ብቻ ስድስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን አክሽፎአል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንም ለኮርፖሬሽኑ የመድህን ዋስትና የሰጠውን የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ካሳ ይከፍለው ዘንድ በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኮስኮ ይገነባለት ዘንድ የኮልፌ ሆስፒታልና የንፋስ ስልክ ሆስፒታል ፕሮጀክቶችን ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ሁለቱንም ፕሮጀክቶች በገባው ውል መሰረት ለመፈፀም ባለመቻሉ የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ቢሮ በቀን 14/06/16 በቁጥር 3ህ/አ አ/ከአ/ዲግ/1785/16 በፃፈው ደብዳቤ ውሉ ተቋርጦ ከሁለቱም የሆስፒታል ፕሮጀክቶች እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ዘጠኝ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የሚሌ - ጋላፊ የመንገድ ፕሮጀክት፤ ከጅቡቲ መንግስት በ43 ሚሊዮን ዶላር ወስዶት የነበረው ጋላፊ -ዲኪል የመንገድ ፕሮጀክት እና ሌሎችም ውላቸው ተቋርጦ ለሌላ ኮንትራክተር እንዲሰጡ ሆኗል፡፡
-መሠረት ሚድያ-





ይህን ሚዲያ አጥብቄ የምወደው
በትክክለኛ መርማሪ ጋዜጠኛ
ስለሚመራ ነው 🙏🙏
Keep it up!!!!