(መሠረት ሚድያ)- በጅቡቲ የባሕር ዳርቻ ከ300 በላይ ስደተኞችን ጭና ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በመስመጧ ምክንያት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ የ139 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ዛሬ አስታውቋል።
በዚህ ሰዓት እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ይህ የተገለጸው የሟቾች ቁጥር በጅቡቲ ባለሥልጣናት አማካይነት የተቀበሩትን ብቻ የሚያካትት ሲሆን ሌሎች በራሳቸው በስደተኞቹ የተቀበሩ ቢኖሩም ባለሥልጣናት የአስክሬኖቹን ሁኔታ አጣርተው እስኪያረጋግጡ ድረስ በይፋዊው የሟቾች ቁጥር ውስጥ እንደማይካተቱ በጅቡቲ የIOM ተልዕኮ መሪ የሆኑት አሌክሳንደር ኩዋሳክ ገልጸዋል።
ኩዋሳክ አክለውም «በጣም የሚያሳዝነው ነገር ስማቸው እንኳን ሳይጻፍ በጋራ መቃብር መሬት ውስጥ መቀበራቸው ነው፤ ልክ በጦርነት ወቅት እንደሚሆነው ሁኔታ። ሁላቸውም እናትና አባት አሏቸው፤ ነገር ግን ምን እንደደረሰባቸው ቤተሰቦቻቸው እስከመጨረሻው ሳያውቁ ሊቀሩ ይችላሉ» ብለዋል።
እንደ ተልዕኮ መሪው ገለጻ ስደተኞቹ ከአራት ቀን በፊት ምሽት ላይ በጀልባዋ የተሳፈሩ ሲሆን ጉዞ በጀመሩ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከባሕሩ ዳርቻ ሳይርቁ መስመጧን ተናግረዋል። የአደጋው ዋና ምክንያትም ጀልባዋ ከመጠን በላይ ሰዎችን አጭና በመጓዟ እንደሆነ ጠቁመዋል።
«የአካባቢው ባለሥልጣናት የተቻላቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል፤ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ወደ ባሕሩ ዳርቻ የሚመጡትን በርካታ አስክሬኖች ማስተናገድ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸው ነበር» ሲሉ ኩዋሳክ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣናት የተረፉትን ስደተኞች በኦቦክ ወደሚገኘው የIOM የሕይወት አድን ማዕከል እያጓጓዟቸው ይገኛሉ። እዚያም የባሕር ውኃ በመዋጣቸው ምክንያት አስፈላጊውን የሕክምና እርዳታ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።
ማዕከሉ ከሄዱት መካከል አንዳንዶቹ የቤተሰብ አባሎቻቸው በአደጋው መሞታቸውን የተረዱ ሲሆን ለሌሎቹ ደግሞ በሕይወት መኖራቸውን ለአገራቸው ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ደውለው እንዲያረዱ የስልክ አገልግሎት ተመቻችቶላቸዋል።
ከአፍሪካ ቀንድ ተነስተው በርካታ ስደተኞች ሥራ ፍለጋ ወደ ባለጠጎቹ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት የሚያደርጉት ጉዞ አደገኛና ተወዳጅ ሲሆን በዚህ የባሕር መስመጥ አደጋ እስካሁን የቢያንስ 84 ሰዎች ደብዛ ጠፍቶ ይገኛል። ይህም አካባቢው ካስተናገዳቸው የከፉ የባሕር ላይ አደጋዎች አንዱ ያደርገዋል።
በኢትዮጵያ ሚድያዎችም ሆነ ባለስልጣናት እስካሁን በዚህ ታላቅ አደጋ ዙርያ የተባለ ነገር የለም።
| መሠረት ሚድያ |


