በአዲስ አበባ የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲጀመር ትዕዛዝ መተላለፉ ተሰማ፣ መምህራን ደግሞ ለሚድያዎች መረጃ እንዳይሰጡ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል
(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገነቡ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች የቦታ ርክክብ ተደርጎ ግንባታ እንዲጀመር ትዕዛዝ መተላለፉ ተሰምቷል።
ከመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ መምህራኑ መረጃዎችን 'ለውጭ አካል' ላሏቸው ሚድያች አሳልፈው እንዳይሰጡ የሚከለክል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ተረድተናል።
መሠረት ሚዲያ የተመለከታቸው የውስጥ መረጃዎችና የፎቶ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በስድስቱም የግንባታ ሳይቶች ላይ የቦታ መለኪያ (XY Coordinate) ርክክብ ተከናውኖ ኮንትራክተሮች ስራ እንዲጀምሩ መመሪያ ተላልፏል።
ከዚህ የሥራ ትዕዛዝ ጎን ለጎንም መምህራኑ በማህበራቸው የቴሌግራም ግሩፖች ላይ የሚያደርጓቸው ውይይቶች ምስጢራዊነታቸው ተጠብቆ እንዲቆይና ለሶስተኛ ወገን በተለይም ለገለልተኛ ሚዲያዎች እንዳይጋለጡ፣ እንዲሁም መብታቸውን የመጠየቅ ሂደቱን ወደ ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳይቀይሩት የሚል ጥብቅና ግልጽ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
መምህራኑ መረጃዎችን ከመንግስት መዋቅር እና ከትምህርት ቢሮ ብቻ እንዲቀበሉ የታዘዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች "የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ያደርጓችኋል" በሚል ቃና የተሰጠው መመሪያ መምህራኑ በገንዘባቸውና በቤታቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን የመጠየቅ መብት የሚገድብ ነው ተብሎ ተተርጉሟል።
ይህ አዲስ መመሪያና የግንባታ ጅማሮ ዜና የወጣው ከስድስት ወራት በፊት በከንቲባ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሠረት ድንጋይ የተጣለለት ፕሮጀክት እስካሁን መሬት ላይ የሚታይ ተጨባጭ ስራ ባለመጀመሩ መምህራኑ በከፍተኛ ምሬትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በሚገኙበት ወቅት ነው።
እነዚህ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ መምህራን ቤቱን ለማግኘት ሲሉ 25 በመቶ የሚሆነውን ቅድመ ክፍያ እንዲከፍሉ በተጠየቁት መሠረት፣ አብዛኛው መምህር የኑሮ ውድነቱን ተቋቁሞ ከወዳጅ ዘመድና ከባንክ ተበድሮ በአጠቃላይ ወደ 3.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ገቢ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ግንባታው በገባው ቃል መሠረት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ርክክብ ባለመደረጉ፣ መምህራኑ ባልተገነባና ገና መሠረቱ ባልወጣ ቤት ለተበደሩት ገንዘብ በየወሩ ከፍተኛ ወለድ እንዲከፍሉ መገደዳቸው የኑሮ ጫናውን አክብዶባቸዋል።
"ባዶ ሆዳችንን እያስተማርንና በኪራይ ቤት እየተሰቃየን፣ በሌለ ቤት ወለድ እየከፈልን መቆየት አልቻልንም" በሚል መምህራኑ ሲያቀርቡት የነበረው አቤቱታ እስካሁን ተገቢውን ምላሽ ከማግኘት ይልቅ አሁን ላይ "ዝም በሉ" የሚል ማስጠንቀቂያ መታከሉ ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል።
መንግስት በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (AASTU) ባለሙያዎች በተገኙበት ግንባታው በይፋ እንደሚጀመር ቢገልጽም፣ መምህራኑ ግን "ይህ በእውነት የግንባታ ጅማሮ ወይስ የጩኸታችን ማፈኛ ስልት?" የሚል ጥርጣሬ አላቸው።
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ማህበራት ስም እስከ 5 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ከመምህራን ተሰብስቦ እስካሁን አንድም መምህር ቤት አለመረከቡ ፕሮጀክቱ ላይ ያለውን አመኔታ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ባለሥልጣናቱ መምህራኑን "መረጃ አትስጡ፣ የግሩፕ ገጻችሁን ዘጉ" ብለው ማዘዛቸው ግልጽነትን የሚያጠፋና በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ የገባበትን ፕሮጀክት ከተጠያቂነት የሚያሸሽ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
መሠረት ሚዲያ የመምህራኑን ድምፅ በማክበርና እውነታውን በመፈለግ ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን የሚቀጥል ይሆናል።
| መሰረት ሚዲያ |





