ከአመት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ታስረው የተወሰዱ 13 ወጣቶች እስካሁን ደብዛቸው ጠፍቶ እንደሚገኝ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- አስራ ሶስት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወጣቶች ደብዛቸው ከጠፋ ነገ የካቲት 8 ቀን 2018 ዓ.ም አንድ ዓመት ይደፍናል።
ወጣቶቹ ታፍነው የተወሰዱት በመከላከያ ሰራዊት እንደሆነ የሚገልፁት ቤተሰቦቻቸው “ከዚያች ቀን በኋላ ልጆቻችንን አየሁ የሚል ጠፋ” ይላሉ።
ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤት ገብተን ልጆቻችን መጥፋታቸውን እና ከቤታቸው የወሰዳቸው መከላከያ ሰራዊት መሆኑን ብናስረዳቸውም “የመከላከያን ስም ለማጥፋት ነው” በሚል አስፈራርተው መለሱን ብለዋል።
“ተስፋ ሳንቆርጥ ወደ ጦር ኃይሎች ምድር ኃይል ግቢ ገብተን ልጆቻችን ቀይ ቦኔት በለበሱ በመከላከያ ኃይል አባላት ነው የወሰዱበት ብለን ስናመለክት ሁለት ቀን በሕንፃው ቢሮ ውስጥ አስረው ለቀቁን ሲሉ ለሚዲያችን ተናግረዋል።
ወደ ፌደራል ፖሊስ እና ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋናው መስሪያ ቤት አቅንተው ስለ ልጆቻቸው ደብዛ መጥፋት የጠየቁት ወላጆች በተመሳሳይ ቀና ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ነው የተናገሩት።
“ከመኖሪያ ቤታቸው በሕግ ትፈለጋላችሁ በሚል የወሰዳቸው የመንግስት አካል ሆኖ ሳለ ስንጠይቅ ለምን ጠየቃችሁ በሚል አሁንም ያስፈራሩናል፣ ለማን አቤት እንበል?” ይላሉ ወላጆቻቸው።
ደብዛቸው ከጠፉት ታሳሪዎች መሀል ገነት አራጌ፣ ሰይፈ ተክለ ጊዮርጊስ፣ አቤል አለምነህ፣ ክፍሎም ሀብቴ፣ ሱራፊል ብሩክ እና ሰብስቤ አለሙ ይገኙበታል።
በወቅቱ ታፍነው ከተወሰዱት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ የሆነው ወጣት አማኑኤል የማነብርሃን ሌላኛው ነበር።
ወጣቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታ ቅርንጫፍ በምክትል ስራ አስኪያጅነት ያገለግል ነበር። የካቲት 10/2017 ዓ.ም ግን ይሰራበት ከነበረው ከዚህ ቅርንጫፍ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተይዞ ተወስዶ እስካሁን ያለበት እንደማይታወቅ ዘመድ ጓደኞቹ በወቅቱ ለመሠረት የሰጡት መረጃ ያሳያል።
ቤተሰቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠ/ሚር ፅ/ቤት፣ ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለፖሊስ እና ለደህንነት ቢሮው አቤት ቢሉም እስካሁን ምንም ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ።
"ማመልከቻውን በመፃፍ ይመለከተዋል የተባለ አካል ጋር ሁሉ መድረስም ብንሞክርም መድረስ አልተቻለም፣ የተቻለዉ ላይም መልስ የለም" የሚሉት ቤተሰቦቹ የወጣቱ ሁለት ልጆቹ በከባድ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለዋል።
የአማኑኤል ጉዳይ እዚሁ ቦታ ለሁለተኛ ጊዜ መፈፀሙ የተረጋገጠ ሲሆን ከእሱ እስር ከሁለት ወር ቀደም ብሎ አንድ የባንኩ ሰራተኛ የሆነ ስራ አስኪያጅ ልደታ ቅርንጫፍ ንግድ ባንክ ዛጉዌ ከቀኑ 5:30 ሰዓት ላይ ስራ ላይ እያለ ጭንብል በለበሱ ሰዎች መወሰዱ ታውቋል።
እንደ ወጣት አማኑኤል ሁሉ በርካታ ዜጎች ከቅርብ ወራት ወዲህ ተይዘው እንደሚሰወሩ፣ አንዳንዶቹ የዲያስፖራ ኮሚኒቲ አባላት እንደሆኑ እንዲሁም ከተያዙ በኋላ ከፀጥታ አካላት ጋር በገንዘብ ተደራድረው የሚለቀቁ እንዳሉ መሠረት ሚድያ ከዚህ በፊት ያቀረባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
አንዳንዶቹ ‘በወቅታዊ ሁኔታ' በሚል እና በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉ ሁኔታዎች ጋር በማገናኘት እንደሚያዙ ታውቋል፣ ሌሎቹ ደግሞ ‘እስከሚጣራ' በሚል ካለምንም ክስ ለበርካታ ሳምንታት እና ወራት በእስር ቤት እንደሚማቅቁ ታውቋል።
“ገድለዋቸውም ከሆነም ዘመድ ጋር አልቅሰን ቁርጡን አውቀን ቤታችን አርፈን እንቀመጥ። እንዴት ልጅን ያህል ነገር ጠፍቶ ቤት ተኝተን እናድራለን?" ሲሉ የቤተሰብ አባላት ለሚዲያችን ተናግረዋል።
-መሠረት ሚድያ-





ያማል።
very very sad this government must foll down ::